ችግኝ የመትከል መርሃ-ግብር ተካሄደ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ሠራተኞች "ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ እንከላከል" በሚል መሪ ቃል የችግኝ መትከል መርሃ-ግብር ሐምሌ 22 ቀን 2009 ዓ.ም አካሄዱ፡፡ በሰበታ ከተማ ተፍኪ አካባቢ በተካሄደው የችግኝ መትከል መርሃ-ግብር ላይ፤ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በየጊዜው መንከባከብ እንደሚያስፈልግ በመርሃ-ግብሩ ላይ የተሳተፉ ሠራተኞች ተናግረዋል፡፡

የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጄኔራል ተክለብርሃን ወ/አረጋይ መርሃ-ግብሩን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአየር ንብረት ለውጥ ኢትዮጵያን ለመሰሉ ኢኮኖሚያቸው በዋናነት በግብርና ላይ ለተመሰረተ አገራት ትልቅ ጉዳትን የሚያስከትል ሲሆን ለዚህም የዛፍ ችግኞችን በመትከል የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሀገራዊ የሳይበር ኃይል የመገንባት ተልዕኳችንን ከመፈጸም ጎን ለጎን እንደ ተቋም በየአመቱ በምናካሂደው የችግኝ መትከል መርሃ-ግብር የሀገራችንን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ እውን ከማድረጋችን በተጨማሪ ሀገራችን እ.ኤ.አ በ2025 በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ የተገነባ መካከለኛ ገቢ ያላት አገርን ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ኢመደኤ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡