አመሰራረት አመሰራረት

ባለንበት የኢንፎርሜሽንና ግሎባላይዜሽን ዘመን ኢንፎርሜሽን የአንድ አገር ቁልፍ የመወዳደሪያ አቅም ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ኢንፎርሜሽን በየትኛውም ዘርፍ ወሳኝ ግብአት እየሆነ መጥቷል፤ ከግል ህይወታችን አንስቶ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ከኢንፎርሜሽን ጋር እጅጉን የተቆራኘ ነው፡፡ ኢንፎርሜሽን በማህበራዊና ፖለቲካዊ ህይወት ውስጥ በተለይም ደግሞ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተጫወተ ባለው ሚና ወሳኝ ኃይል እና ቁልፍ ሃብት ሆኖ ለመቆጠር አስችሎታል፡፡ ኢንፎርሜሽን በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት ላይ ቁልፍ ሚናን ሊጫወት የሚችለው ደህንነቱ ተረጋግጦ ለሚፈለገው ዓላማ ብቻ ሲውል እንደሆነ እሙን ነው፤ በተቃራኒው ኢንፎርሜሽን ደህንነቱ ካልተረጋገጠ ከኃይልና ሃብትነቱ ይልቅ ለልማት ማደናቀፊያነትና ለጸረ-ዲሞክራሲያዊ ተግባር የመዋል እድሉ ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም አገራት የኢንፎርሜሽንን ቁልፍ ሚና በመረዳት ለደህንነቱ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ውሎ አድሯል፡፡ የኢንፎርሜሽን ደህንነት ሲባል የኢንፎርሜሽኑን ሚስጥራዊነት፣ ምልዑነት እና ተደራሽነት ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያም የኢንፎርሜሽንን ቁልፍ ሃብትነት ከወዲሁ በመረዳት ለደህንነቱ፤ በአጠቃላይም ኢንፎርሜሽን ለሚከማችበት፣ ለሚተነተንበትና ለሚሰራጭበት የሳይበር ምህዳር ደህንነት ልዩ ትኩረት ሰጥታ በመንቀሳቀስ ላይትገኛለች፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ ሳይበር ከሁለንተናዊ ሀገራዊ ፍላጐቶች እና ፍልስፍናዎች ጋር እንዲጣጣም ማድረግ የሚል ዓላማ አስቀምጣ እየሠራች ትገኛለች። ይህም ሳይበር ሀገራችን ለያዘቻቸው የልማት፣ የዲሞክራሲ እና የሠላም መርሐ ግብሮች አሳላጭ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ይህንን ቁልፍ ሀገራዊ ፍላጎት መሰረት በማድረግ፤ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ብቃት ያለውና በሀገሪቱ ህዳሴ ቁልፍ ሚናን የሚጫወት ብሔራዊ የሳይበር ኃይል የመገንባት ራዕይ አስቀምጦ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ኢመደኤ  ለመጀመሪያ ጊዜ በ1999 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 130/1999 መሠረት ተቋቋመ፡፡ ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ የመጣውን የሳይበር ወንጀል ለመከላከል እና ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ የኤጀንሲውን ተግባር እና ኃላፊነት እንደገና ማሻሻል በማስፈለጉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 250/2003 እንዲሁም በድጋሚ በ2006 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 808/2006 የኤጀንሲው ተግባሮች እና ኃላፊነቶች ተሻሽለው እንደገና ሊቋቋም ችሏል፡፡