በቴሌቪዥን ዲጂታላይዜሽን ሃገር አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራ ዙሪያ ውይይት ተደረገ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢ.መ.ደ.ኤ) በቴሌቪዥን ዲጂታላይዜሽን ዙሪያ ከፌደራልና ክልሎች ከተውጣጡ የመንግስትና የግሉ የሚዲያ አካላት ጋር ለግማሽ ቀን የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡  በውይይቱም ሃገሪቱ በምታደርገው ከአናሎግ ወደ ዲጂታል የቴሌቨዥን ስርጭት ሽግግር ባለድርሻ አካላት በዋናነት በትግበራ ፕላትፎርሙ ላይ በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ተነስቷል፡፡ ፕሮጀክቱ ወደ ስራ በሚገባበት ወቅት በ22 የስርጭት ጣቢያዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን ከአናሎግ ወደ ዲጂታላይዜሽን የሚደረገው ሽግግርም በ2010 ዓ.ም በሙከራ ደረጃ እንደሚጀምርና በቀጣይ እንደሚሰፋ ነው የተገለጸው፡፡ በውይይቱ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን ወ/አረጋይ መልስ ሰጥተውበታል፡፡ ኢ.መ.ደ.ኤ ለቴሌቪዥን ዲጂታላይዜሽን ፕሮጀክት ትግበራው DVB-T2  ቴክኖሎጂን እንደሚጠቀም የታወቀ ሲሆን ይህም የቴሌቪዥን ስርጭቱ በጥራትም ሆነ ከደህንነት አንጻር አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንደሚያደርገው ነው የተገለጸው፡፡ ፕሮጀክቱ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ መግባቱ የሚታወቅ ነው፡፡