በመንግስትና በቁልፍ የግል ተቋማት የሳይበር ደህንነት አቅም ለመፍጠር የሚያስችል ስታንዳርድ ፀደቀ

ኢመደኤ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባራት መካከል የኢንፎርሜሽንና ኮምፒዩተርን መሰረት ያደረጉ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ብሄራዊ የፖሊሲ የህግ፣ የስታንዳርድና ስትራቴጂ ረቂቆችን የማዘጋጀትና ሲፀድቁም ተፈፃሚነታቸውን መከታተል አንዱ ነው፡፡ በቅርቡ ኤጀንሲው በመንግስትና በቁልፍ የግል ተቋማት የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስታንዳርድ (Critical Mass Cyber Security Requirement Standard) በስራ ላይ እንዲውል በዋና ዳይሬክተሩ አፅድቋል፡፡ ስታንዳርዱ ተቋማት የኢንፎርሜሽን ደህንነት ስጋቶችን መቆጣጠር እንዲችሉ ወሳኝ የሳይበር ደህንነት አቅሞችን እና ሂደቶችን (Capabilities and Processes) ቀጣይነቱን ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ እንዲገነቡ የሚያስችል ነው:: ስታንዳርዱ ከሳይበር ደህንነት አመራር፣ አገዛዝ እና አስተዳደር (leadership, governance and management) እንዲሁም ከሰው ሃይል እና ቴክኖሎጂ አንፃር መፈጠር ያለባቸውን አቅሞች የሚያስቀምጥ ሲሆን የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ሂደቶችንም አጠቃልሎ ይዟል፡፡ ስታንዳርዱ በመንግስትና በቁልፍ የግል ተቋማት ተግባራዊ መደረግ ያለበት (አስገዳጅ) ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በመጀመሪያው ዙር ለተካተቱ ተቋማት እና ለሌሎች ባለ ድርሻ አካላት እየተሰራጨ ይገኛል፡፡ በቀጣይም ስታንዳርዱ ሌሌሎች ተቋማት የሚደርስ ሲሆን በስታንዳርዱ ዙሪያ ጥልቅ ግንዛቤ እና አቅም በመፍጠር ተግባራዊነቱን ለማገዝ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና አቅም ግንባታ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተገልጧል፡፡ ስታንዳርዱን በዚህ ገፅ ላይ ማግኘት ይችላሉ፡፡ http://www.insa.gov.et/web/en/documents