በደህንነት ቁጥጥር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ወደ አገር በሚገቡና ከአገር በሚወጡ የመረጃና የመረጃ መገናኛ መሳሪያዎች የደህንነት ቁጥጥር (Security Inspection) ዙሪያ እንዲሁም በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ዙሪያ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በፍተሻ ስራ ላይ ለተሰማሩ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ባለሙያዎች እና በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡ ስልጠናው ከህዳር 05/2009 ዓ.ም እስከ ህዳር 08/2009 ዓ.ም በተከታታይ ለአራት ቀናት ያህል ተሰጥቷል፡፡ የስልጠናው ዋና ዓላማ ወደ አገር በሚገቡና ከአገር በሚወጡ የመረጃና የመረጃ መገናኛ መሳሪያዎች በኩል ሊደርስ የሚችልን ተጋላጭነት፣ ስጋትና አደጋ በጋራ በመከላከል ብሔራዊ ደህንነትን ማረጋገጥ እንደሆነ በስልጠናው ወቅት ተገልጿል፡፡ ኢመደኤ በአዋጅ ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች መካከል ወደ አገር የሚገቡና ከአገር የሚወጡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች፣ የመረጃ አነፍናፊዎችና የጥቃት ቴክኖሎጂዎች በአገር ደህንነት ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ ከመከላከል አንጻር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት መቆጣጠር አንዱ ነው፡፡