ኢመደኤ ብሔራዊ የሳይበር መከላከል ልዩ የተሰጥኦ ውድድር አዘጋጀ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) በአይነቱ ልዩ የሆነና በሳይበር መከላከል ዙሪያ ልዩ ተሰጥኦ ላላቸው ኢትዮጵያዊያን በሙሉ (ከ18 አመት በላይ፣ በማንኛውም ጾታ እና በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ) የቀረበ የሳይበር መከላከል ልዩ የተሰጥኦ ውድድር ማካሄድ ጀመረ፡፡ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ የሚያስችል ምዝገባ ከታህሳስ 03/2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ 21/2009 ዓ.ም በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ምዝገባውም በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እና በኢመደኤ ዋናው ቢሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የመመዝገቢያ ፎርሙ በኤጀንሲው ዌብ ፖርታል www.insa.gov.et ወይም  በፌስቡክ ገጽ https://www.facebook.com/cybertalentethiopia ላይ  የሚገኝ ሲሆን ይህንን ፎርም በመሙላትና ወደ cybertalentethiopia@insa.gov.et  በመላክም መመዝገብ ይቻላል፡፡

በዚህ ውድድር ላይ በመጨረሻ ተመርጠው ለሚቀርቡ 30 ታለንቶች አለም አቀፍ ስታንዳርድ የጠበቀ የሳይበር መከላከል ልዩ ልማት ፕሮግራም አካል የሚሆኑ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ በዘርፉ ታለንት ካላቸው ባለሙያዎች ጋር አብሮ የመስራት ዕድል እና ሌሎች ተጨማሪ ዕድሎችም የሚያገኙ ይሆናል፡፡

በውድድሩ ዙሪያ የበለጠ መረጃ ለማግኘት www.cte.insa.gov.et ወይም www.insa.gov.et መጎብኘት ይቻላል፡፡