በማሕበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት ለግብይት ሊቀረብ የተዘጋጀ ሕገ-ወጥ ሸቀጣሸቀጥ ተወረሰ

በማህበራዊ ሚዲያ ግብይት የተፈፀመባቸውና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አደገኛ፣ ሕገ-ወጥና ተመሳስለው የተመረቱ ሸቀጣሸቀጦች  በታላቋ ብሪታኒያ አቋርጦ ወደ ሌላ አካባቢ ሊያመሩ ሲሉ ተይዘው እንደተወረሱ ቢቢሲ ባወጣው መረጃ ገለጸ፡፡ ሸቀጣሸቀጡ በቁጥጥር ሥር የዋለው በብሪታኒያ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ወንጀል ምርመራ ቡድን ከፖሊስ ጋር ባደረገው ከፍተኛ የክትትልና የማጣራት ሥራ በተገኘ መረጃ ነው ተብሏል፡፡ ይህን ተከትሎ ህብረተሰቡ ሕጋዊነት የጎደላቸው ነጋዴዎች ፌስቡክንና ኢንስታግራምን ተጠቅመው የሚያቀርቧቸውን ዕቃዎች ሲገዛ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው የአገሪቱ የሕገ-ወጥ ንግድ ተቆጣጣሪ ቡድን መሪ ግርሀም ሞግ አስጠንቅቀዋል፡፡ በዚህ አይነት መንገድ በፈረንጆቹ ታህሳስ ወር ብቻ ለገበያ የቀረቡ 83ሺ የሚደርሱ የተለያዩ ሕገ-ወጥ ሸቀጣሸቀጦች በብሪታኒያ ኤርፖርቶች እንደተያዙም አያይዘው ገልጸዋል፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞ በበዓላት ሰሞን ሸማቾች ለሚገዙት ዕቃ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡

http://www.bbc.com/news/business-38415206