የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ስፖርት ለሁሉም” ውድድር ተጀመረ

7ኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስፖርት ለሁሉም ውድድር ታህሳስ 22 ቀን 2009 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በድምቀት ተጀመረ፡፡ በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ  የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) የስፖርት ልዑክ አባላት የተካፈሉ ሲሆን፤ እንደ ባለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮም ኤጀንሲው በተለያዩ የስፖርት ውድድሮች የሚሰተፍ ይሆናል፡፡  

በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አቶ ዘነበ ተሰማ እንደተናገሩት፤ የውድድሩ ዓላማ በዋናነት ማንኛውንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ የአካልና የአእምሮ ጤንነትን ማሳደግ ነው ብለዋል፡፡ ውድድሩ ጤንነቱ  የተጠበቀ አምራች ዜጋ ለማፍራት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ኤምባሲዎች እና የግል ድርጅቶች በ46 የስፖርት አይነቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡ በመክፈቻው በተካሄደ የእግር ኳስ ጨዋታ የመብራት ኃይል ሰራተኞች ቡድን ጀኔራል ዊንጌት ቴክኒክና ሙያን 3 ለ 1 አሸንፏል፡፡