በቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) በቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅ ቁጥር 761/2004 ዙሪያ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡ ስልጠናው ጥር 6 ቀን 2009 ዓ.ም ለግማሽ ቀን ያህል የተሰጠ ሲሆን፤ በስልጠናው ላይ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች ፕሬዝዳንት አቶ በላቸው አንችሳ እንዲሁም የኢመደኤ ም/ዋ/ዳይሬክተር ሻለቃ ቢኒያም ተወልደ ተገኝተዋል፡፡

በስልጠናው ላይ በአዋጁ ዙሪያ የሚስተዋሉ የህግ ክፍተቶችን በተመለከተ አጭር ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ በአዋጁ ዙሪያ የሚታዩ ቴክኒካል ጉዳዮችን በተመለከተ (ወንጀሉ ስለሚፈጸምባቸው መሳሪያዎች፣ ወንጀለኞች እንዴት የማጭበርበር ስራውን እንደሚሰሩ፣ ከምርመራ ጋር በተያያዘ የደረሱ ኪሳራዎችን እንዴት ማስላት እንደሚቻል ወ.ዘ.ተ) በኢመደኤ ባለሙያዎች ማብራሪያ ለመስጠት ተችሏል፡፡

በአዋጁ አፈጻጸም ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተመለከተ ከዳኞች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን፤ በቀጣይም በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ በመድረስ ስልጠናው ተጠናቋል፡፡