በወሳኝ አቅም ሳይበር ደህንነት ስታንዳርድ ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሄደ

በወሳኝ አቅም ሳይበር ደህንነት ስታንዳርድ ዙሪያ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጋር የካቲት 15 ቀን 2009 ዓ.ም የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) በመንግስትና ቁልፍ የግል ተቋማት የሳይበር አቅም ለመፍጠር የሚያስችል የወሳኝ አቅም ሳይበር ደህንነት ስንዳርድ (Critical Mass Cyber Security) ያዘጋጀ ሲሆን፤ ይህ የውይይት መድረክም ባለድርሻ አካላት በስታንዳርዱ ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ ስታንዳርዱን በሚተገብሩበት ሁኔታ ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ እና ተቋማት በስታንዳርዱ ላይ ያላቸውን እይታ በመረዳት አዋጭ የትግበራ ስልት ለመንደፍ የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጀነራል ተክለብርሃን ወ/አረጋይ በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት የዚህ ስታንዳርድ መዘጋጀት የተቋማትን የኢንፎርሜሽንና ሳይበር ደህንነት ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፤ ይህም ሊሆን የሚችለው ሁሉም ተቋማት በስታንዳርዱ መሰረት የሳይበር ደህንነትን የሚያረጋግጥ የኢንፎርሜሽን ደህንነት የስራ ሂደት ማቋቋም እንዳለባቸው ከዚህም በተጨማሪ የሰው ኃይል አቅም እና የአሰራር ስርአት መዘርጋት እንደሚጠበቅባቸው፤ ለዚህ ደግሞ የየተቋማቱ አመራር ለስታንዳርዱ ተፈጻሚነት የመሪነት ሚናን መጫወት ሲችል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የስታንዳርዱን አጠቃላይ ጭብጥ በተመለከተ አቶ ተመስገን ቅጣው፡ በኢመደኤ የብሔራዊ ኢንፎርሜሽን ደህንነት ማኔጅመንት ማዕከል ኃላፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ተሳታፊዎችም በስታንዳርዱ አጠቃላይ ይዘት እና አተገባበር ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በቀጣይም በስታንዳርዱ ዙሪያ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር መሰል የውይይት መድረኮች እንደሚዘጋጁ ተገልጿል፡፡