አገራዊ የቴሌቪዠን ስርጭትን ከአናሎግ ወደ ዲጅታል ለማሸጋገር የሚያስችሉ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተገለጸ

አገራዊ የቴሌቪዠን ስርጭትን ከአናሎግ ወደ ዲጅታል ለማሸጋገር እየተደረገ ባለው ጥረት የስርጭት እና የመቆጣጠሪያ ማዕከሎች ግንባታ ተጀምረው በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም የዲጅታል ስርጭቱን ለመጀመር የሚያስችሉ ነባር የዩ.ኤች.ኤፍ የማሰራጫ ጣቢያዎች የአቅም ደረጃን ወደ ዲጂታል ለማሳደግ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር አዳዲስ የማሰራጫ ጣቢያዎችን ለማቋቋም የሚረዱ ጥናቶች ተጠናቀው ወደ ትግበራ መገባቱም ተገልጿል፡፡ አሁን ደግሞ የዲጅታላይዜሽኑን የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማረጋገጥ የቴክኒካል ስራን ከሚሰራው ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር የውል ስምምነት ተፈርሟል፡፡ ደርጅቱ ጌትስ ኤር የተሰኘ የአሜሪካን ዓለም አቀፍ ኩባንያ ሲሆን ስምምነቱን የመንግስት ግዠ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን በመወከል ከድርጅቱ ጋር ተፈራርሟል፡፡ በዚህ መሰረት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የቴክኒክ ስራውን ለማከናወንም ከድርጅቱ ጋር  ተፈራርሟል፡፡ አገራዊ የዲጅታል ቴሌቪዠን ስርጭት የቴክኒካል ስራ በመጋቢት ወር የሚጀመር ሲሆን በአስር ወራት እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል፡፡ የፕሮጀክቱ ዕውን መሆን ጥራቱ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና በሁሉም ቦታ ተደራሽ የሚሆን የዲጂታል ቴሌቪዠን ስርጭት አገሪቷ እንዲኖራት ያስችላታል፡፡ በአጠቃላይ በስምምነቱ መሰረት ከ34 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡