ዩሮፖል በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች የሚፈፀም የሳይበር ወንጀል የተደራጀ ወንጀልን እንደሚያባብስ ገለጸ

የአውሮፓ ፖሊስ ቢሮ ዩሮፖል (Europol) በአሁኑ ሰዓት በጣም አደገኛ እና አሳሳቢ ከሆኑ የተቀናጁ ወንጀሎች መካከል የሳይበር ወንጀል ከቀዳሚዎቹ አምስት የወንጀል ስጋቶች ውስጥ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡ ከተቀናጁ የሳይበር ጥቃቶች መካከልም የዶክመንት ማጭበርበር፣ የገንዘብ ማታለል፣ በህገ-ወጥ የኦንላይን ንግድ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል ያለው ተቋሙ፤ ከፍተኛ የሆኑ ተግዳሮቶችን ለህግ አስፈጻሚው አካል እንደደቀኑበት በሪፖርቱ አትቷል፡፡ "አደገኛ እና የተቀናጁ የወንጀል ስጋቶች ግምገማ" በሚል ርእስ ባወጣው የጥናት ሪፖርት የጥቃት መጠኑ ከቀን ወደ ቀን እያደገ የመጣ ሲሆን የህብረተሰቡ የቢዝነስ እንቅስቀሴዎች፣ የህዝብ አገልግሎት መስጫዎች፣ እንዲሁም የምንጠቀማቸው መሳሪያዎች ከኢንተርኔት ጋር የተያያዙ እና ዲጂታላይዝ እየሆኑ ከመምጣታቸው ጋር ችግሩ እንደሚያያዝ ገልጿል፡፡ ተቋሙ በሪፖርቱ የተለያዩ አይነት የሳይበር ወንጀሎችን ያተተ ሲሆን ከእነዚህ መካከልም የራንሰምዌር ጥቃት ፣ የማልዌር ጥቃቶች ፣ በኔትዎርክ ላይ የሚፈጸም ጥቃት፣ የክፍያ ካርድ ማጭበርበር እና የኦንላይን ጾታዊ ጥቃቶች ይገኙበታል ብሏል፡፡ ወንጀለኞችም በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ጥቃታቸውን እንደሚፈጽሙ ተቋሙ የገለጸ ሲሆን ከኢንተርኔት ጋር ግንኙነት ያላቸውን መሳሪያዎች የሚጠቀሙ አካላት የጥንቃቄ መጠናቸውን ሊያሳድጉ ይገባል ሲል መክሯል፡፡

http://www.ibtimes.co.uk/europol-claims-high-tech-cybercrime-fuelling-organised-crime-1610803