ፌስቡክ የመረጃዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጫ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አሳወቀ

በማህበራዊ ሚዲያ ኔትዎርኮች አማካኝነት የሃሰት ዜናዎች ስርጭቶች መስፋፋታቸውን ተከትሎ ፌስቡክ፣ ጉግል እና ቲዊተርን የመሳሰሉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከገቡ ሰነባብቷል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ፌስቡክ የሃሰት መረጃዎች ስርጭትን ለመከላከል የሶስተኛ ወገን ትክክለኛነት ማረጋገጫ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አሳውቋል፡፡ አሁን በተቋሙ ተግባራዊ የሆነው ቴክኖሎጂ የሃሰት መረጃዎችን አከራካሪ ይዘት "disputed content" በሚል የሚያሳውቅ መሆኑም ታውቋል፡፡ ፌስቡክ ለመጀመሪያ ጊዜ አከራካሪ ይዘት በሚል ማሳወቂያ የለጠፈው "በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አየርላንዳዊያን ወደ አሜሪካ በባርነት መጥተዋል" የሚል  ይዘት ያለው መረጃ ላይ መሆኑን አሳውቋል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ስለ ጽሁፉ ይዘት ምንም እውቀት ሳይኖራቸው ለሌሎች የማካፈል ልምድ እንዳላቸው የጠቀሰው ፌስቡክ ገለልተኛ በሆኑ አካላት የመረጃዎቹን ይዘት በመለየት የተዛቡ ከሆኑ "አከራካሪ ይዘት" የሚል ማሳወቂያ እንደሚሰጥ ጠቁሟል፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ በተወሰኑ ተጠቃሚዎች ላይ ሙከራውን እንዳደረገ የተጠቆመ ሲሆን ይህ ሁኔታም በተቋሙ ላይ ሊነሱ የሚችሉትን የተለያዩ አስተያያቶች እና ነቀፋዎች ቀንሶለታል ተብሏል፡፡ ፌስቡክም በቀጣይነት በእያንዳንዱ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

https://www.theguardian.com/technology/2017/mar/22/facebook-fact-checking-tool-fake-news