ኢመደኤ ከሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጥናትና ምርምር ሥራ ስምምነት ተፈራረመ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ከመሬት አስተዳደር ጋር የተገናኙ ውሳኔዎችን በሥነ-ምድር (Geospatial) እውቀት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ በማስቻል ረገድ የራሱ ድርሻ ያለው እና በመስኩ ብሔራዊ አቅምን ለመፍጠር የሚያስችል አቅጣጫ ጠቋሚ ሳይንሳዊ ጥናት ለማካሄድ ከሦስት ዩኒቨርሲቲዎች (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና መቐለ ዩኒቨርሲቲ) ጋር ውል ተፈራረመ፡፡

ሦስት ሚሊዮን ብር ይፈጃል የተባለው ጥናቱ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ሲጠናቀቅ ሀገሪቱ በዘርፉ አሁን ያለችበትን ደረጃ እና ወደፊትም ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስችላትን ዘርፈ-ብዙ አቅም መፍጠር የሚያስችላትን አቅጣጫ ይጠቁማል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ኢመደኤ ይህንን ጥናት በገንዘብ እንደሚደግፈው በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡  

ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ኮሎኔል ታዜር ገ/እግዚአብሔር፡ የኢመደኤ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የጂኦስፓሻል መረጃና ደህንነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንደተናገሩት ከመሬት ጋር የተያያዙ ውሳኔዎች በእውቀት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ የሥነ-ምድር መረጃ እውቀት አስፈላጊ በመሆኑ ኢመደኤ ጥናቱን በገንዘብ የሚደግፍ መሆኑን ገልጸው ሌሎች ተቋማትም ይህን ፈለግ መከተል እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ ም/ዋ/ዳይሬክተሩ አያይዘውም ጥናቱ ሲጠናቀቅ በመስኩ ሀገራችን ያለችበትን ደረጃ እና የወደፊት አቅጣጫ በማመልከት ለስትራቴጂ ቀረጻ ግብዓት ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር አስናቀ መኩሪያ፡ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ምድር መረጃና ቴክኖሎጂ ማዕከል ዳይሬክተር በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲዎች በኩል በመስኩ የሚደረገውን ጥናት በሚፈለገው ጥራት ሰርቶ ለማቅረብ አቅም ያላቸው መሆኑንና ዝግጁም መሆናቸውን ጠቅሰው እንደ ኢመደኤ ያሉ ተቋማት በተለያዩ መስኮች ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተባብረው መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ተካ፡ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ምድር መረጃና ክትትል ሳይንስ ተቋም ዳይሬክተር በበኩላቸው የጂኦስፓሻል ትምህርት በሀገራችን በተወሰኑ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በድህረ-ምረቃ ደረጃ ብቻ የሚሰጥ በመሆኑ ሀገሪቱ በመስኩ ኢንዳስትሪው በሚፈልገው መጠን አቅም አልገነባችም ያሉ ሲሆን፤ ከዚህ አኳያ ምን አይነት አቅጣጫ መከተል እንደሚገባ ጥናቱ እንደሚጠቁም ገልጸዋል፡፡

ኢመደኤ ጨምሮ ስድስት የሚሆኑ የትምህርት እና የምርምር ተቋማት ያሉበት የጂኦስፓሻል ኢንዳስትሪ-ዩኒቨርሲቲ ፎረም ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡