ብሔራዊ የጋራ እና የተቀናጀ የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት ፕላትፎርም ተዘጋጀ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) በመንግስት በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት ኢትዮ ሳት (ETHIOSAT) የተሰኘ ብሔራዊ የጋራ እና የተቀናጀ የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት ፕላትፎርም አዘጋጀ፡፡ ፕላትፎርሙ ከሚያዚያ 13 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ አምስት የቴሌቪዥን ቻናሎችን ይዞ የሙከራ ትግበራ ጀምሯል፡፡ የፕላትፎርሙ መገኛ አድራሻ፡ Satelite: E8WB፣ Frequency፡ 11512፣ FEC: 2/3፣ Symbol Rate: 30Mbuad፣ Polarization: Vertical፣ Modulation: 8PSK ነው፡፡  

በተመሳሳይ ዜና በፕላትፎርሙ አፈጻጸም ዙሪያ ከክልል መስተዳድር እና የከተማ አስተዳደር ተወካዮች እንዲሁም የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሃን ጋር የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡     

ኢትዮ ሳት ፕላትፎርም የሚዲያ እኩልነትንና ፍትሃዊነትን እንዲሁም ተደራሽነትን በማረጋገጥ በመረጃ የበለጸገ ማህበረሰብ በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚናን የሚጫወት ነው፡

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከ15 እስከ 20 የሚሆኑ የቴሌቪዥን ቻናሎች በየግላቸው ሳተላይት በመከራየት የሚያሰራጩ ሲሆን፤ ፕላትፎርሙ ተግባራዊ ሲሆን ግን ሁሉም የቴሌቪዥን ቻናሎች በአንድ ፕላትፎርም እንዲያሰራጩ እድል የሚሰጥ ይሆናል፡፡ በዚህም የቴሌቪዥን ቻናሎች ለሳተላይት ኪራይ የሚያወጡትን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረቱም ባሻገር፤ የደህንነት ተጋላጭነትን በማስቀረት፣ የሚዲያ ተደራሽነትን በማረጋገጥ እንዲሁም ከሞገድ አጠቃቀም ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ፕላትፎርሙ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ በሌላም በኩል ሁሉም የህዝብና የመንግስት የቴሌቪዥን ቻናሎች በፕላትፎርሙ የሚያካተቱ ሲሆን፤ ከብሮድካስት ባለስልጣን የማሰራጫ ፍቃድ የተሰጣቸውና ፕላትፎርሙን መጠቀም ለሚፈልጉ የሃገር ውስጥ የግል የቴሌቪዥን ቻናሎች እንዲካተቱ ክፍት የሚሆን ነው፡፡