ኢመደኤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) በሳይበር ደህንነት የድህረ-ምረቃ መርሃ-ግብር (Masters Program) ለመጀመር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ከአዲስ አበባ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የመቐለ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር ተፈራረመ፡፡ ስምምነቱ በሳይበር ኢንዳስትሪ ውስጥ ብቁ የሆኑ የሳይበር ፕሮፌሽናሎችን ለማልማት እንደ መነሻ የሚወሰድ እንደሆነ በኢመደኤ የሳይበር ታለንት ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ሻለቃ ሠላምይሁን አደፍርስ ገልጸዋል፡፡ በሀገሪቱ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የለማ በቂ የሰው ኃይል እንደሌለ የገለጹት ዳይሬክተሩ ይህንን ክፍተት ከመመለስ አንጻር ኢመደኤ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት ዶ/ር ኢሳያስ ገ/ዮሃንስ እንደገለጹት የድህረ-ምረቃ ትምህርቱን ለመጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተካሄደ ሲሆን፤ በሚቀጥለው የትምህርት በጀት አመት ፕሮግራሙ እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡ በተለይም ይህን የድህረ-ምረቃ ፕሮግራም ለየት የሚያደርገው በማንኛውም የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው በዚህ ፕሮግራም ላይ መሳተፍ የሚያስችላቸው አግባብ መኖሩ እንደሆነ ዶ/ር ኢሳያስ ገልጸዋል፡፡

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የመቐለ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት አቶ መለስ ገብረየስ በበኩላቸው የሳይበር ኢንዳስትሪ የደረሰበት ደረጃ እና በዘርፉ በሀገሪቱ ያለው የሰው ኃይል አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ ያልተመጣጠነ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህ ስምምነት ይህንን ክፍተት ከመሙላት አንጻር ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡