ለሳይበር ደህንነት ታለንት ልማት ትኩረት መሰጠት እንደሚገባ ተጠቆመ

የኦፕን ዌብ አፕሊኬሽን ደህንነት ፕሮጀክት (Open Web Application Security Project- OWASP) ጥናት ይዞት በወጣው መረጃ መሰረት በአውሮፓ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የሰለጠነ የባለሙያ እጥረት እንዳለ ይፋ አድርጓል፡፡ የሳይበር ኢንዳስትሪ ከእለት ወደ እለት በከፍተኛ ደረጃ እያደገና እየተለዋወጠ የሚሄድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሀገራት በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያ በማልማት በኩል ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ፕሮጀክቱ ጠቁሟል፡፡ ፕሮጀክቱ በመጪው ግንቦት የሚያካሂደውን ኮንፈረንስ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ በአህጉረ አውሮፓ ለሚገኙና በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ፍላጎት ላላቸው ግለሰቦች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠትና ልዩ ድጋፍ በማድረግ ብቃታቸውን ማሳደግ ያስፈልጋል የሚሉ አጀንዳዎችን ይዞ እንደሚቀርብ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ጋሪ ሮቢንሰን ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የታላቋ ብሪታንያ ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ማዕከል የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ በማስቀመጥ፤ የሀገሪቱ ባለስልጣናት እና ፖለቲከኞች ለሳይበር ደህንነት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው አሳስቧል፡፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ የተለያዩ ሴሚናሮችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንደሚሰራም ማዕከሉ ጠቅሷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ታላቋ ብሪታንያ ለሳይበር ደህንነት የሚውል 1.9 ቢሊዮን ፓውንድ በመመደብ በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኝ ማዕከሉ የጠቀሰ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ለሳይበር ታለንት ልማት የሚደረግ ኢንቨስትመንት እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ በዚህም የሳይበር ደህንነት ትምህርት ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ እንዲሰጥ እና ከ14 አመት በላይ ያሉ ታዳጊዎች የሳይበር ደህንነት ክህሎቶችንና እውቀቶችን ተግባራዊ እያደረጉ እንዲሄዱ ትኩረት እንደሚሰጥ ማዕከሉ ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) በኢትዮጵያ ያለውን የሳይበር ደህንነት የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ መሰረት የሚጥል በሳይበር ደህንነት የድህረ-ምረቃ ፕሮግራም ለመጀመር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ጋር መፈራረሙ ይታወሳል፡፡    

http://www.itproportal.com/features/developing-europes-cyber-security-talent-pipeline/