በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመከላከያና ደህንነት ልዩ ኮሚቴ አና ሁለት ቋሚ ኮሚቴዎች በኢመደኤ የሥራ ጉብኝት አካሄዱ

በክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃም፡ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የተመራ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ልዩ ኮሚቴ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን (ኢመደኤ) የሥራ እንቅስቃሴ ጎበኘ፡፡

የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጀ ተክለብርሃን ወ/አረጋይ ስለ ኤጀንሲው አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ለልዩ ኮሚቴው ገለጻ አድርገዋል፡፡ ሀገራዊ የሳይበር ደህንነትን ከማረጋገጥ አንጻር ሀገራዊ የሳይበር ስፔስ መገንባት ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህንን ከማድረግ አኳያ ኤጀንሲው በሰው ኃይል ልማት፣ በህግ ማዕቀፍ ዝግጅት፣ በስታንዳርድ ዝግጅት፣ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን በማረጋገጥ እና በመሳሰሉት ጉዳዮች መሰረት የሆኑ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ለልዑካኑ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በተለይም በሳይበር ኢንዳስትሪ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ እና ሀገራዊ የሳይበር ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተለመደው አካሄድ የማይቻል ሲሆን፤ በፍጥነት መዝለል (Leapfrog) እንደሚያስፈልግ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

ልዩ ኮሚቴው በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር የቀረበለትን ገለጻ ካደመጠ በኋላ የተቋሙን ተጨባጭ የሥራ ውጤቶች ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፡፡

በመጨረሻም ኤጀንሲው የሀገሪቱን የሳይበር ደህንነት ከማረጋገጥ፡ እንዲሁም አገር በቀል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከማልማት አንጻር አበረታች ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ የልዩ ኮሚቴው መሪ አቶ አማኑኤል አብርሃም ገልጸዋል፡፡ የኤጀንሲውን የሥራ እንቅስቃሴ በመደገፍ ረገድ የልዩ ኮሚቴው ድጋፍ እንደማይለይም አቶ አማኑኤል ገልጸዋል፡፡