በኢንተርኔት የታገዘ የመማር ማስተማር ሥርዓት ለአህጉሪቱ የትምርት ጥራት መሻሻል ወሳኝ ነው ተባለ

የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) በተለይም ደግሞ ኢንተርኔት በአፍሪካ የትምህርት ስርአት ላይ ወሳኝ የሆነ አወንታዊ ሚናን እንደሚጫወት የኢንተርኔት ማህበረሰብ ጥናት ሪፖርት አመለከተ፡፡ በዩኔስኮ (UNESCO) አስተባባሪነት በሩዋንዳ ኪጋሊ የተካሔደው የኢንተርኔት ማህበረሰብ ኮንፈረንስ አህጉሪቱ ዘርፉን ያገናዘበ የትምህርት ሥርዓት መዘርጋት እንዳለባት መክሯል፡፡ በኮንፈረንሱ ላይ እንደተገለጸው የአህጉሪቱን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በኢንተርኔት የታገዘ የመማር ማስተማር ሥርዓትን ማስፈን ውጤታማ ያደርጋል ተብሏል፡፡ ይህም የትምሕርት ሥርዓቱን ከሚቀርጹ አካላት ሳይቀር ይሁንታን አግኝቶ በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት ያስፈልገዋል ነው የተባለው፡፡ በምክክሩ ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ባቀረቡት ጥናት እንዳሉት የአፍሪካ የትምሕርት ሥርዓት ከኢንተርኔት ጋር ያለው ቁርኝት፣ ከሌሎች ከበለጸጉ አገራት እየወሰደ ያለው ልምድና የመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች የተካተቱ ሲሆን ፖሊሲ አውጭዎችም የራሳቸውን ሚና መጫዎት እንዳለባቸው አመላክቷል፡፡ በፈረንጆቹ 2016 ዓ.ም 341 ሚሊዮን አፍሪካውያን የኢንተርኔት አገልግሎት የሚጠቀሙ መሆኑን ያወሳው መረጃው ይህም በኢንተርኔት የታገዘ ትምርት ለመስጠት መልካም አጋጣሚ ነው ብሏል፡፡ በምክክሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ኢንተርኔት ማህበረሰብ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳዊት በቀለ በበኩላቸው በኢይ.ሲ.ቲ ዘርፍ ክህሎት ያለው ሰው ማፍራት የአህጉሪቱን ችግሮች ለመፍታትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪ ለማድረግ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡  ይህም የተባበሩት መንግስታት በ2030 ያቀደውን የትምህርት ግብ ለማሳካት እንደ መነሻ እንደሚሆን ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡ በኢንተርኔት የታገዘ ትምህርት በቀላሉ ሁኔታዎችን ለመረዳት ትልቅ መሳሪያ ሲሆን፤ ትምህርትን በቀላል ወጭ ለማዳረስ፣ የማስተማሪያ ቁሳቁሶችን ተክቶ ለማስተማርና  ለመሳሰሉት ጥቅሞች አሉት ተብሏል፡፡

http://www.biztechafrica.com/article/connected-learning-key-improving-education-africa-/12436/