የሳይበር ደሕንነት የምርምርና የውድድር ማዓከል ሊቋቋም ነው

የአውሮፓ ሕብረት የሳይበር ደህንነት አቅምን ለማሳደግ የምርምርና የውድድር ማዕከላትን ከማቋቋም ጀምሮ በቴክኖሎጂ ላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስና ከአገራት ጋር የጠበቀ ግንኙነትን በመፍጠር ስጋቱን እንደሚከላከል አስታወቀ፡፡ ሕብረቱ ይህን እንዲያደርግ የተገደደው በየጊዜው የሚደርሰውን የሳይበር ጥቃት ተከትሎ ሲሆን ይህም ኢሮፖል (Europol) ባወጣው መረጃ መሰረት በሳይበር ጥቃት ምክንያት በአውሮፓ በዓመት 265 ቢሊዮን ዩሮ ኪሳራ ይደርሳል ተብሏል፡፡ ከዚህም ሌላ በአህጉሩ በግልና በሕዝብ ተቋማት የሚታየው ጉዳት አሁን ካለበት እስከ ፈረንጆቹ 2019 በአራት እጥፍ እንደሚያድግ ተጠቁሟል፡፡ አህጉሩን ከጥቃት ለመታደግ የመጀመሪያ ዕቅድ መርቀቁን ያብራራው ዘገባው ጠበቅ ያለ የሕግ ከለላ መተግበር፣ የሳይበር ጥቃትን የተመለከቱ ጥናትና ምርምሮችን አቅም ማጎልበትና የሳይበር ኢንዱስትሪውን ማበረታታት የሚሉት በረቂቁ የተካተቱ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ኳንተም ቴክኖሎጂን (quantum technologies) መሰረት ያደረገ ትውልድ መቅረጽና ዘመናዊ ግብይትን ማስፈን በዕቅዱ ውስጥ የሚገኙ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሕብረቱ ደሕንነትን ማረጋገጥ ("duty of care") የሚል መርህ በመዘርጋት እ.ኤ.አ 2018 መጀመሪያዎቹ ወራት ዕቅዱን እንደሚያስፈጽም ኮሚሽኑን ዋቢ አድሮጎ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

እንደ ዘገባው በዕቅዱ ውስጥ ከሚገኙ ተግባራቶች መካከል አንዳንዶቹ በአባል አገራትና በሕብረቱ ፓርላማ መጽደቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡

http://www.reuters.com/article/us-europe-cybercrime/eu-looks-to-extra-spending-diplomacy-to-bolster-cyber-security-idUSKCN1BH2Y1