የሳይበር ኢንሹራንስ ደንበኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

ባሳለፍነው ግንቦት 2017 ከደረሰው የዋናክራይ (WannaCry) ጥቃት በኋላ የሳይበር ኢንሹራንስ ደንበኞች ቁጥር በተለያዩ አህጉራት እያደገ መምጣቱን ሮይተርስ ይዞት በወጣው ዘገባ ገለጸ፡፡ የአሜሪካውን የኢንሹራንስ ኩባንያ ኤ.አይ.ጂ (American International Group Inc - AIG.N) ዋቢ አድረጎ ሮይተርስ እንደዘገበው በቻይና እና በሌሎችም የኢሲያ አገሮች የደንበኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል ሲል አስነብቧል፡፡ ጉዳዩ ወሳኝ መሆኑን የሚያወሳው ዘገባው የቁጥሩ ማደግ በአሜሪካን አገር 87 በመቶ የደረሰ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ወደ 38 በመቶ ማሻቀቡን አውስቷል፡፡ የኤ.አይ.ጂ የቢዝነስ ክፍል ኃላፊ ሲንዚያ ዙ ለሮይተርስ እንደተናገሩት የሳይበር ኢንሹራንስ ደንበኞች ቁጥር መጨመር ምክንያቱ ተቋማት በሳይበር ጥቃት የሚደርስባቸውን ጉዳት በተመለከተ ግንዛቤያቸው እያደገ በመምጣቱ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህም ባሳለፍነው ግንቦት በተከሰተው የዋናክራይ ጥቃት በ150 አገራት ከ200ሺህ በላይ ኮምፒተሮች መጠቃታቸውን እንዳብነት ያነሳሉ፡፡ እንደዘገባው ከሆነ የዓለም የሳይበር ኢንሹራንስ ገበያ በአሁኑ ጊዜ እስከ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድረሱንና የደንበኞች ቁጥርም በዓመት በአማካይ ከ20 እስከ 25 በመቶ እንደሚያድግ ጠቅሷል፡፡ የሳይበር ጥቃትን ተከትሎ የሚመጣው ኪሳራ በ2015 ብቻ 400 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድረሱንም መረጃው ሳያስታውስ አላለፈም፡፡

https://www.reuters.com/article/us-fidelity-investments-bitcoin-idUSKBN1AP0AO