ሴቶች በቴክኖሎጂው ዘርፍ ቢሳተፉ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ አንድ ጥናት ጠቆመ

ሴቶች በቴክኖሎጂው የስራ መስክ በስፋት ቢሳተፉ ከፍተኛ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ተጠቆመ፡፡ ሰሞኑን ዘጋርዲያን ከሶስት የዓለማችን የዘርፉ ውጤታማ ሴቶች ጋር ቆይታ አድርጎ ለአንባቢያን ባበቃው ዘገባ የቴክኖሎጂው የስራ መስክ የጾታ እኩልነት የሚጎድለው መሆኑን አስታውሷል፡፡ የኸግል (Huggle) መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆነችው ቫለሪ ስታርክ ከዘጋርዲያን ጋር ባደረገችው ቆይታ "በሴቶች የሚመራ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ለውጥ ለማስመዝገብ ብዙ ጊዜ አይወስድም፤ ምክንያቱም ሴቶች ከፍተኛ የማህበረሰብ ኃላፊነትና ስሜት ስለሚንጸባረቅባቸው ነው"  ብላለች፡፡ እንደ ቫለሪ ስታርክ የጾታ እኩልነትን ያገናዘበ የቴክኖሎጂ ዓለም መፍጠር ምርትን ለማሳደግም ሆነ ለእያንዳንዳችን ተጠቃሚነት አይነተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ሌላዋ ዘጋርዲያን ያነጋገራት ሴት ደግሞ ጀሲካ ናዚሪ (Jessica Naziri) ስትሆን፤ በቴክኖሎጂው የትምህርት መስክ የሴቶችን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ የሚሰራውን ድርጅት ቴክሴሽ ዶት ኮ (TechSesh.co) መስራች ናት፡፡ እሷ እንደምትለው የቴክኖሎጂ ኢንዳስትሪዎች ከማጭበርበር ይልቅ ለሴቶች አመች የሆኑ አገልግሎት ሰጭ ምርቶችን በማቅረብ የሴቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልግል፡፡ ማብራሪያ የተጠየቀችው  ሦስተኛዋ ሴት አን ማሬ ኢማፊዶን (Anne-Marie Imafidon) ስትሆን በኢንተርኔት የሚደረገውን የቃላት ጥቃት ማስቆምና ቴክኖሎጂውን ለበለጠ ጥቅም እንዲውል ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ትላለች፡፡ ከዚህ አኳያ ሁሉም እንዳስገነዘቡት ሴቶች በቴክኖሎጂው የስራ መስክ በስፋት ቢሰማሩ ለማህበረሰቡ ችግር ፈች የሆኑ አዳዲስ ግኝቶችን ስራ ላይ ለማዋል ያላቸው ብቃት ከፍተኛ ስለሆነ ኩባንያዎች ሁኔታዎችን ማመቻቸትና እድል መስጠት እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

https://www.theguardian.com/careers/blog/2017/oct/12/gender-parity-women-tech-equality-workforce