አዲስ የሳይበር ጥቃት መከሰቱ ተገለጸ

ባድራቢት (BadRabbit) የተሰኘ አዲስ የኮምፒውተር ማልዌር (malware) በአንዳንድ አገራት ላይ መከሰቱ ተገለጸ፡፡ በተለይም ጥቃቱ በሩሲያ በከፍተኛ ደረጃ የተከሰተ ሲሆን፤ ዩክሬን፣ ቡልጋሪያ፣ ቱርክ እና ጃፓን ሌሎች የጥቃቱ ሰለባ አገራት መሆናቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡ አዲሱ የሳይበር ጥቃት በፍጥነት ሁሉንም የዓለም አገራት የማዳረስ አቅሙ ከፍተኛ እንደሆነና በከፍተኛ ደረጃ የተቀናጀ የጥቃት አይነት መሆኑን የኢሴት (ESET) የሳይበር ደህንነት ኩባንያ ከፍተኛ ተመራማሪ ሮበርት ሊፖቭስኪ ገልጸዋል፡፡ ጥቃቱ የሚያነጣጥረው እንደ ትራንስፖርት ኦፕሬተሮች የመሳሰሉ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን ሲሆን ይህም ሌሎች ተቋማትን በቀላሉ ለመቆጣጣር እንዲያመች የታለመ መሆኑን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ የሩሲያው ኢንተርፋክስ (Interfax) የዜና ወኪል፣ የዩክሬኑ ኦዴሳ (Odessa) አየር መንገድ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ተቋማት ሲሆኑ፤ በተለይም የዩክሬኑ ኦዴሳ አየር መንገድ በደረሰበት ጥቃት የተወሰኑ በረራዎችን ለመሰረዝ መገደዱን ተገልጿል፡፡ ሁኔታው ያሳሰበው የአሜሪካ መንግስት በሰጠው መግለጫ እንዳሳወቀው ሁሉም የአገሪቱ ተቋማትና ግለሰቦች ከአዲሱ የጥቃት ማዕበል እንዲጠነቀቁና ችግር ከተከሰተም በፍጥነት ለፌዴራል የምርመራ ቢሮ (FBI)  እንዲያመለክቱ ለዜጎቹ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ባድራቢት ከዚህ በፊት ተከስቶ ዓለምን በቢሊዮን የሚገመት ዶላር ካሳጣው ዋናክራይ (WannaCry) ጋር ተመሳሳይነት ያለውና መረጃዎችን በመቆለፍ የማስለቀቂያ ገንዘብ የሚጠይቅ የማልዌር አይት ነው ተብሏል፡፡

http://www.reuters.com/article/us-ukraine-cyber/new-wave-of-cyber-attacks-hits-russia-other-nations-idUSKBN1CT21F