የራንሰምዌር ጥቃት የዓለም ሥጋት ሆኖ ይቀጥላል ተባለ

የሶፍትዌር እና የሀርድዌር ደህንነት ኩባንያው ሶፎስ (Sophos) ደረስኩበት ባለው ጥናት መሰረት ራንሰምዌር (ransomware) የኮምፒውተር ቫይረስ በሚቀጥሉት ጊዜያትም የዓለም ሥጋት ይሆናል ሲል አስታወቀ፡፡ ኩባንያው በላብራቶሪው አማካኝነት እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከሚያዝያ 1/2017 እስከ ጥቅምት 3/2017 ባደረገው ጥናት መሰረት ራንሰምዌር ከሌሎች የማልዌር አይነቶች በተለየ ሁኔታ ከዚህ ቀደም እንዳደረሰው ሁሉ በቀጣይም ከፍተኛ ኪሳራ ያደርሳል ሲል በሪፖርቱ አስነብቧል፡፡ ሪፖርቱን ዋቢ አድርጎ አይቲኒውስአፍሪካ (itnewsafrica.com) እንደዘገበው በሚቀጥሉት ጊዜያትም ራንሰምዌር አደገኛና ለመከላከል ውስብስብ ባህሪ ያለው ጥቃት አድራሽ ቫይረስ ሆኖ ይዘልቃል ብሏል፡፡ ማልዌሩ ከዚህ በፊት ሲያደርስ ከነበረው ጉዳት በተጨማሪ ሲስተምን የማጥቃት ባህሪ እንደተላበሰ የላብራቶሪ ምርመራው ያሳያል ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ተከስቶ የነበረው የራንሰምዌር አይነት ዋናክራይ (WannaCry) ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሱ የሚታወቅ ሲሆን፤ አሁን በአዲስ መልክ የተከሰተውና የተወሰኑ አገራትን ያጠቃው ባድራቢት (BadRabbit) እና ኖትፔትያ (NotPetya) ከዋናክራይ በላይ የከፋ እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡ አዲሱ የራንሰምዌር አይነት ከአደገኛነቱ በተጨማሪ መቼና በምን ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ እንኳን በግልጽ ለማወቅ ያዳግታል ተብሏል፡፡ ይህም ሙሉ በሙሉ የኮምፒውተር ስርዓቱን በመጉዳት ከፍተኛ ኪሳራ ሊያደርስ ከሚችለው በተጨማሪ ሌላ የማጥቂያ መንገድ ሊከተል እንደሚችልም ታውቋል፡፡

የራንሰምዌር ጥቃት ከዚህ ቀደም ከነበረው ሌላ የስማርት ስልኮችን ጨምሮ ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ስርዓትን ሊጎዳ እንደሚችል የኩባንያው ላቦራቶሪ ተንበዮዋል፡

 http://www.itnewsafrica.com/2017/11/no-platform-is-immune-to-ransomware/