የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም የሳይበር ወንጀልን የመቋቋም ብቃታቸው የተሻለ ነው ያለቸውን አገራት ይፋ አደረገ

በዓለማችን የሳይበር ወንጀለኞች እየተራቀቁና የጥቃታቸውን አድማስ እያሰፉ በመጡበት በዚህ ወቅት የሳይበር ወንጀልን መከላከል ቀጠሮ የማያስፈልገው ጉዳይ ነው ሲል የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም (World Economic Forum) በድረ-ገጹ ላይ አስነብቧል፡፡ ወንጀለኞች ከግለሰብ ጀምሮ ለዓለም ወሳኝ በሆኑ ተቋማት ላይ የሚያደርሱት ጥቃት እያሻቀበ ከመሄዱም በላይ ጥቃቱን ለማድረስ በሰኮንዶች ውስጥ የመፈጸማቸው ፍጥነት ስጋቱን ከምንም በላይ እንደጨመረ ዘገባው ይጠቅሳል፡፡ ሆኖም የወንጀለኞች የማጥቃት ጥበብ እንዲህ ሲራቀቅ ዓለም ችግሩን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት ግን ከአደጋው ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ዘገባው ጠቅሷል፡፡  ወንጀለኞች ጥቃት ለማድረስ አዳዲስና እንደሁኔታው የሚተጣጠፍ ፈጠራ ይዘው የሚቀርቡ ሲሆን ለመከላከል የሚደረገው ዘመቻ ግን ኋላቀርና ችግሩን የመቋቋም አቅም የሌለው ነው፡፡ በመሆኑም ወንጀለኞች እየተራቀቁ በመጡ ቁጥር ዓለም መስራት ያለበትን ማወቅና ችግሩን መቋቋም የሚችል የቴክኖሎጂ ዕውቀት በመጨመር የደህንነት መከላከያ እና መሰል አሰራሮችን ማጠናከር ያስፈልጋል ሲል ፎረሙ ጠቅሷል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በዓለም የሳይበር ወንጀልን በመከላከል ብቃታቻው የተሻሉ ያላቸውን 20 አገሮች የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም በድረ-ገጹ ያስነበበ ሲሆን፤ በዚህም አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያና ማሌዥያ ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ 

በመሆኑም አንዳንድ አገሮች ችግሩን ለመከላከል በጥቂቱም ቢሆን ከእንቅልፋቸው እንደተነሱት ሁሉ ሌላውም የዓለም አገር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ አለበት ሲል ፎረሙ አሳስቧል፡፡

https://www.weforum.org/agenda/2017/11/cybercrime-how-we-should-fight-criminals