የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብ ውይይት ተደረገ

በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሳይንስ፣ መገናኛና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም የሕግ፣ የፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጋራ በመሆን በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ተዘጋጅቶ የቀረበውን የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ረቂቅ አዋጅ ከተመለከቱ በኋላ ሕዝባዊ ውይይት እንዲደረግበት መወሰናቸውን ተከትሎ ማክሰኞ ሕዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም በረቂቅ አዋጁ ላይ የሕዝብ አስተያየት/ውይይት ተደርጓል፡፡ በቀጣይም ከሕዝብ አስተያየት የተሰበሰቡ ግብአቶችንና ማሻሻያዎችን በማካተት ረቂቅ አዋጁ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አዋጁን ለማዘጋጀት መነሻ ከሆኑ አበይት ጉዳዮች መካከል በዋናነት ከኤሌክትሮኒክ የመረጃ ልውውጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶችን እና የደህንነት (የመተማመን) ስጋቶችን ለማስቀረት ነው፡፡ አዋጁ ለኤሌክትሮኒክስ ፊርማ እውቅና የሚሰጥ ነው፡፡

የኤሌክትሮኒክ ፊርማ በኦንላይን የሚደረጉ መልእክቶችን፣ ግንኙነቶችን ወይም የንግድ ልውውጦችን የተሳታፊዎችን ትክክለኛ ማንነት ለመለየትና ለማረጋገጥ፣ የመልዕክቶችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፣ በምስጠራ ቁልፎች አማካኝነት ሚስጥራዊነትን ለመጠበቅ እንዲሁም መካካድን ለማስቀረት የሚያገለግል አሰራር ነው፡፡

ረቂቅ አዋጁ የኢመደኤን የሕግና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ የተዘጋጀ ነው፡፡