በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዲቫይሶች በየጊዜው ለሳይበር ደህንነት ችግር ይጋለጣሉ

በዓለም ላይ በሳይበር ጥቃት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዲቫይሶች በየጊዜው ከጥቅም ውጭ መሆናቸው ቢታወቅም ችግሩን ለመከላከል እየተወሰደ ያለው እርምጃ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ተባለ፡፡ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም በድረ-ገጹ ባሰራጨው ዘገባ እንዳመለከተው ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት የሳይበር ደሕንነት ስጋት እንደ ችግር ሳይቆጠር ቢቆይም ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ ግን የዓለም ማህበረሰብ  የስጋት ምንጭ እየሆነ መጥቷል ይላል፡፡  የኢንተርኔት ጥቅም  ከኢኮኖሚያዊ፣ ከማህበራዊና ከፖለቲካዊ አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ቢሆንም አብሮ እያደገ የመጣው የሳይበር ጥቃት ሁኔታውን ውስብስብ ማድረጉንም መረጃው ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡ ችግሩ እየገዘፈ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የዘርፉ ባለሙያዎች በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የራሱ የሆነ ሕግና መመሪያ መውጣት አለበት ብለው ጥሪ ቢያቀርቡም ጉዳዩ አሁንም ሰሚ አግኝቶ ወደ መሬት የወረደ ተግባር አልታየም ተብሏል፡፡ የዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ ኢንተርኔት ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ ከመሆኑም ሌላ አሰራሩ ቀላል፣ ፈጣን፣ ርካሽ፣ ድብቅ እና የመሳሰሉት ባህሪዎቹ በሕግ ለመዳኘት ማስቸገሩን ሪፖርቱ አውስቷል፡፡ ይህንኑ አስመልክተው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ባስተላለፉት መልዕክት ሳይበር ምህዳሩን ተከትሎ በሰዎች ላይ እየደረሰ የሚገኘው ጉዳት እንዳሳሰባቸውና ይህን ለመከላከል የወጡ ስምምነቶች ተግባራዊ መሆን አለባቸወ ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸው በዘገባው ተካቷል፡፡

በፈረንጆቹ 1996 በዓለም ላይ 36 ሚሊዮን (1%) የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ግማሽ የሚጠጋው (3.7 ቢሊዮን) የዓለም ሕዝብ የኢንተርኔት ደንበኛ መሆኑ ችግሩ ምን ያክል ግዙፍ ሊያደርገው እንደሚችል በዘገባው ተብራርቷል፡፡

https://www.weforum.org/agenda/2018/03/how-will-new-cybersecurity-norms-develop