የአሕጉሩን ዲጂታል የንግድ ግብይት ለማጠናከር የሚደረገውን ጉባኤ ኢትዮጵያ ልታስተናግድ ነው

በአፍሪካ ዲጂታል የንግድ ግብይት ለመፍጠር የሚመክር ጉባኤ ከግንቦት 23-24/2010 ዓ.ም ለ2 ቀናት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው ተባለ፡፡ በአሕጉሩ ነፃ የንግድ ቀጠና ለማቀላጠፍ ዲጂታል የንግድ ግብይት ማጠናከር መልካም እድሎችን እንደሚያመጣ የጠቀሰው ዘገባው በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች የሚደረጉ ግብይቶች በአፍሪካ ገበያ አዳዲስ ደንበኞችንና ምርት ይዞ እየመጣ ያለ ዘርፍ እንደሆነ የመንግስታቱ ድርጅት አመልክቷል፡፡ ይህም ከሚቀጥሉት ከአምስት እስከ አስር ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ በአፍሪካ በዲጂታል ኤሌክትሮኒክስ የሚደረጉ ግብይቶች በዓመት እስከ 75 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዢንዋን ጠቅሶ በድረ-ገጹ አስነብቧል፡፡

በጉባኤውም የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ሲቪል ማህበራት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ባለሃብቶች፣ ምሁራን፣ የወጣቶችና ሴቶች ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚሳተፉም ታውቋል፡፡

http://www.xinhuanet.com/english/2018-05/22/c_137198551.htm