የአውሮፓ ህብረት የሽብር ይዘቶችን በአንድ ሰዓት ውስጥ በማያስወግዱ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ቅጣት ሊጥል ነው

አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 14/2010

የአውሮፓ ህብረት የሽብር መረጃዎችን እና ይዘቶችን ከፕላትፎርሞቻቸው ላይ በአንድ ሰዓት ውስጥ በማይሰርዙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ የገንዘብ ቅጣት ሊጥል እየተዘጋጀ መሆኑን አሳውቋል፡፡

በዚህም ህብረቱ ፌስቡክን እና ዩቲዩብን የመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሃሰት መረጃዎችን እና ፕሮፖጋንዳዎችን በ60 ደቂቃ ውስጥ እንዲሰርዙ የሚያስገድድ አዲስ እና ጠንካራ ህጎችን ለማውጣት እየተዘጋጀ መሆኑን የፋይናንሽያል ታይምስ ዘገባ አስፍሯል፡፡ 

የአውሮፓ ህበረት የደህንነት ኮሚሽን የሆኑት ጁሊያን ኪንግ የቴክኖሎጂ ተቋማት የሃሰት መረጃዎችን እና የሽብር ፕሮፖጋንዳዎችን በመግታት አመርቂ የሚባሉ ለውጦችን አለማምጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም የህዝቦችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ጠንካራ የሆኑ ህጎችን ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ኪንግ ከዚህ በኋላ አጥፊ እና በስውር የሴራ መረጃዎች ላይ ትእግስት እንደማይኖራቸው አሳውቀዋል፡፡

በፓሪስ፣ ሎንዶን እና በርሊን በቅርቡ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ወዲህ የአውሮፓ ህብረት ተግባር የቴክኖሎጂ ምህዳሮችን እና የማህበራዊ ሚዲያ የግንኙነት መረቦችን ከሽብር መረጃዎች መፈንጫነት የነጻ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡

https://www.theverge.com/2018/8/20/17758542/eu-terrorist-content-legislation-facebook-youtube-takedown