“የሳይበር ደህንነታችን መጠበቅ ለሀገራችን ሰላም ወሳኝ ነው፡፡” ክብርት ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የኢፌደሪ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር

 

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 15/ 2011- በሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ሙፈሪያት ካሚል የሚመራው የልኡካን ቡድን በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) በመገኘት ጉብኝት አድርጓል፡፡

በኤጀንሲው ጉብኝት ያደረጉት ክብርት ሚኒስትሯን ጨምሮ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታዎች አቶ ዘይኑ ጀማል እና አቶ ከፍያለው ተፈራ ከኢመደኤ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

አሁን ባለንበት ዘመን ሃገራት የሳይበር ደህንነታቸውን ካላስጠበቁ ሰላምን ማስጠበቅ ከባድ እንደሚሆንባቸው ሚኒስትሯ አስምረውበታል፡፡

በውይይቱ ወቅትም ኢመደኤ ራዕዩን መሰረት  በማድረግ የተሻለ ስራዎችን መስራት እንዲችል እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ሳይበር ምህዳሩን በመጠቀም ሰላማችንን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ነገሮችን መለየት እና መከላከል በሚችል መልኩ የበለጠ የማዘመን ተግባር እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

ኢመደኤ ከዚህ ቀደም በመንግስት እና በህዝብ የተሰጡት ሃላፊነቶች እንዳሉት የገለጹት ክብርት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ጊዜው የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ እንዲታጠቅ በማድረግ በተሻለ ደረጃ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ይሰራል ብለዋል፡፡

ተቋሙ በአብዛኛው በወጣቶች የተገነባ በመሆኑ በተሻለ አቅም አዳዲስ አሰራሮችን በቀላሉ የሚለምድ እና በብቃት መፈጸም የሚችል ከመሆኑም በላይ ሃገራችን የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ በተሻለ ለማስቀጠል የተሻለ እገዛ ይደርጋል ሲሉ አክለዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህነንት ኤጀንሲ አዲስ ለተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር ተጠሪ ከሆኑ ተቋማት አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡