የግንቦት 20 27ኛ አመት የድል በዓል በኢመደኤ ተከበረ

የግንቦት 20 27ኛ አመት የድል በአል "የላቀ ብሔራዊ መግባባትና ዲሞክራሲያዊ አንድነት፤ ለላቀ አገራዊ ስኬት" በሚል መሪ ቃል ዓርብ ግንቦት 17/2010 ዓ.ም በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አጀንሲ (ኢመደኤ) ተከበረ፡፡ በእለቱ ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የውይይት መነሻ ሃሳብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በመነሻ ጽሑፉ የፌደራሊዝም ጽንሰ-ሀሳብ፣ ያስመዘገባቸው ስኬቶች፣ ያጋጠሙት ተግዳሮቶቹና መፍትሔዎቹ በሚል ርዕስ የቀረበው መወያያ ጽሁፉ ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ስኬቶችን ማስመዝገቡ ተጠቁሟል፡፡ ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ የቡድን መብቶች እንዲከበሩ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ፣ ሕብረ-ብሔራዊነት እንዲያብብና የመሳሰሉትን ስኬቶች ማጣቱም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡ ባለፉት 27 አመታት የፌደራል ስርአቱ ከገጠሙት ተግዳሮቶች መካከልም  የዲሞክራሲ አለመጎልበት፣ አክራሪ ብሔርተኝነት፣ ልዩነትን አለመቀበልና የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ሲሆን የዚህ መፍትሔ ሊሆን የሚችለውም ልዩነትን በውይይት መፍታት፣ የሕዝብ ተሳታፊነትን ማረጋገጥና መሰል እንቅስቃሴዎች ችግሩን ሊያስወግዱት እንደሚችሉ ተጠቅሳል፡፡

የኢመደኤ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ፍቅሬ በእለቱ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የመንግስት ስርዓት ሲዘረጋ ከነበረው ታሪክ በመነሳት፣ የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በመመልክትና በመሳሰሉት ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የተለያዩ እምነቶች፣ ወጎች፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የመሳሰሉት ባሉበት አገር ፌደራሊዝም አስፈላጊነቱ የማያጠራጥር ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና  የኢመደኤ ም/ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት አቶ ወርቁ ጋቸና (ቀደም ብለው ከተሸሙት ሁለቱ ም/ዋና ዳይሬክተሮች፤ ሌ/ኮሎኔል አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እና አቶ ተፈሪ ፍቅሬ በተጨማሪ) በዕለቱ ተገኝተው ከአባላት ጋር ተዋውቀዋል፡፡