ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ልታዘጋጅ ነው
Aplicacions anidades
Publicador de continguts
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን የሚያዘጋጁት ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ (Ethiopian Tech Expo - ETEX 2025) ከግንቦት 8 እስከ 10/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ፡ አዲስ አለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ይካሄዳል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በጋራ በመሆን ሁነቱን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ የሁነቱን ዓላማ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለዓለም ማበርከት የምትችለውን እምቅ አቅም በማሳየት የአፍሪካ ብሎም የአለም የቴክኖሎጂ የስሕበት ማዕከል መሆን የሚያስችላትን እምቅ አቅም ለማሳየት ሁነቱ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡፤ በቴክኖሎጂ ዘርፍ አፍሪካን ለማስተሳሰር ኢትዮጵያ ምቹና አስቻይ ከባቢ እየገነባች መሆኑን ለማመላከት ኤክስፖው ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እና ስኬቶች ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ እና ትስስሮችን ለማጎልበት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፍ የኢትዮጵያን መልካም ስምና ገጽታ ለመገንባት ኤክስፖው መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ (Ethiopian Tech Expo - ETEX 2025) ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ በተለያዩ የቴክኖሎጂ መስኮች ያስመዘገበችውን ስኬት ለማሳየት፣ በተለይም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ላይ እንደ ሀገር ያገኘናቸውን ውጤቶች ለማስተዋወቅ የሚያስችል መድረክ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር እንደ ሀገር በቴክኖሎጂው መስክ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ መስጠት የምንችለውን እምቅ አቅም ለማስተዋወቅና ቀጣይ ትስስሮችን ለመፍጠር የኤክስፖው መካሄድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ በኤክስፖው ላይ አፍሪካ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እንዲሁም በሌሎች ክሱት ቴክኖሎጂዎች ያላትን አቋም ለማንጸባረቅ የሚያስችሉ የፖሊሲ ውይይት መድረኮች እንደሚካሄዱም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ (Ethiopian Tech Expo - ETEX 2025) በ5 ዋና ዋና መስኮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚካሄድ ሲሆን፤ እነዚህም በሳይበር ደህንነት፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት(AI)፣ ፋይናንስ ቴክኖሎጂ (FinTech)፣ ስማርት ከተማ (Smart City)፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ትምህርት (Tech Education) ላይ ያተኮሩ ሲሆን ይህም ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ እና ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ጋር ተጣጣሚነት ያለው ነው::
የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ (Ethiopian Tech Expo - ETEX 2025) ከግንቦት 8 እስከ 10/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ፡ አዲስ አለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል (Addis International Convention Center) ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ በመጀመሪያው የመክፈቻ ቀን ከሳይበር ደህንነት ጋር የተያያዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መርሃ ግብሮች ይከናወናሉ፡፡ በሁለተኛው ቀን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዙሪያ ላይ ያተኮሩ መርሃ ግብሮች የሚከናወኑ ይሆናል፡፡ በሦስተኛው ቀን አጠቃላይ ለሕብረተሰቡ ለጉብኝት ክፍት የሚሆን ሲሆን ሌሎች የመዝጊያ መርሃ ግብሮች የሚከናወኑ ይሆናል፡፡