ቋንቋዎቻችን በዲጂታሉ ዓለም ዳታ ውስጥ የሚቀመጡበትን ቴክኖሎጂ ማበልጸግ በዘመናችን የዲጂታል አብዮት ውስጥ የራሳችን ቦታ እንዲኖረን እንደሚያስችል ተገለጸ
ቋንቋዎቻችን በዲጂታሉ ዓለም ዳታ ውስጥ የሚቀመጡበትን ቴክኖሎጂ ማበልጸግ በዘመናችን የዲጂታል አብዮት ውስጥ የራሳችን ቦታ እንዲኖረን እንደሚያስችል ተገለጸ
የሀገራችን ቋንቋዎች በዲጂታሉ ዓለም ዳታ ውስጥ የሚቀመጡበትን ቴክኖሎጂ ማበልጸግ በዘመናችን የዓለም ዲጂታል አብዮት ውሰጥ ተነጥለን ወደኋላ እንዳንቀርና የራሳችን ቦታ እንዲኖረን የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ።
"ቋንቋ፣ ባህል እና ቴክኖሎጂ ለዕድገት" በሚል መሪ ሀሳብ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ በጋራ ሁለተኛውን አገር አቀፍ የቋንቋ እና ባህል ጉባኤ አካሂደዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋራ በመሆን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በዲጂታል ምህዳሩ ላይ ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተሠራበት እንደሚገኝም በጉባኤው ላይ ተገልጿል።
ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች፣ ባህሎች እና ማንነቶች በአሁኑ እና በመጭው ዘመን ሁለንተናዊ መገልገያ እና መወዳደሪያ መድረክ በሆነው የዲጂታል ቴክኖሎጂ እና የሳይበር ዓለም በአግባቡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ብሎም ውክልና እንዲኖራቸው ለማስቻል፤ በቋንቋ፣ ባሕል እና ቴክኖሎጂ ላይ የሚደረገው ጥናትና ምርምር ከፍ ያለ ፋይዳ እንደሚኖረው በጉባኤው ተመላክቷል።
ለዚህም በመንግሥት፣ በባህል እና ቋንቋ ላይ የሚሠሩ ተቋማት እና በምሁራን መካከል ቅርርብና በትብብር መሥራት ለጉባኤው ዓላማ ስኬት ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ተገልጿል።