የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን እና ለኢመደአ የእስልምና ተከታዮች በሙሉ 1 ሺህ 446ኛውን የኢድ-አል አድሃ (አረፋ) በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸዉ በመላዉ ህዝበ ሙስሊም ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የኢድ-አል አድሃ (አረፋ) በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታና የበረከት በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢድ-አል አድሃ (አረፋ) የእዝነት፣ የመተሳሰብ፣ የመደጋገፍ እና ያለንን ለሌሎች በማካፈል የምናከብረው በዓል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የዘንድሮውን በዓል ስናከብር ኢትዮጵያዊያን ከምንታወቅባቸው ድንቅ እሴቶቻችን መሀል የመደጋገፍ በተለይም በፈተና እና በችግር ወቅት የመረዳዳት ባህላችን መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በዓሉን ስናከብር በተለያዩ ምክንያት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን ያለንን በማካፈል አለኝታነታችንን የምናሳይበት መሆን ይኖርበታል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የበዓላት ወቅት ከሌሎች ጊዜያት በተለየ መልኩ ማህበረሰባችን በከፍተኛ ደረጃ ግብይት የሚፈጽሙበት፤ የሚፈጸመው ግብይትም በአብዛኛው በሞባይል ባንኪንግና በበይነ መረብ አማካይነት መሆኑና ሰፊ የመልዕክት ልዉዉጦች መኖራቸዉን ተከትሎ የዲጂታል ማጭበርበሮች እንደሚጨምሩ ገልጸዋል።
ለዚህም ማህበረሰባችን ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ሊደርሱ ከሚችሉ የዲጂታል ማጭበርበሮች እራሱን ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም በዓሉ የፍቅር፣ የሰላም፣ የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዒድ ሙባረክ!