በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን የተመራ ልዑክ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ጎበኘ
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን የተመራ ልዑክ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ጎበኘ
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን የተመራ ልዑክ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በመገኘት ጉብኝት አደረገ፡፡ የልዑካንን ቡድኑን የተቀበሉት የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ሀገራዊ የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ በተቋም ደረጃ እየተሰሩ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ምን እንደሚምስሉ ለልዑካን ቡድኑ አስጎብኝተዋል፡፡ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው ሁሉን አቀፍ የትብብር ሥራ በቀጣይም በላቀ ደረጃ እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑን የመሩት በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ፤ በተለይም ደግሞ የቴክኖሎጂና የእውቀት ባለቤትነትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ስራ መስራቷን ከጉብኝቱ መረዳታቸዉን አንስተዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነቷንና ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በምታደርገዉ ጥረት ሩሲያ ያላትን ልምድ ከማካፈል ጀምሮ በጋራ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት አምባሳደሩ አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያን ልምድ ለመመልከት ወደ አስተዳደሩ የመጣዉ የዘርፉ ባለሞያዎች ልዑክም ዓላማ የሁለቱን ሃገራት በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር መሆኑን አምባሳደሩ አብራርተዋል፡፡