የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የኢመደአን የዲጂታል ፎረንሲክና የሳይበር ወንጀል ምርመራ ማዕከል ጎበኙ
የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የኢመደአን የዲጂታል ፎረንሲክና የሳይበር ወንጀል ምርመራ ማዕከል ጎበኙ
በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራ የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ቡድን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የዲጂታል ፎረንሲክና የሳይበር ወንጀል ምርመራ ማዕከልን ጎበኘ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ልዑካን ቡድኑ አቀባበል ያደረጉ ሲሆን በአስተዳደሩ እየተገነባ የሚገኘውን የዲጂታል ፎረንሲክና የሳይበር ወንጀል ምርመራ ማዕከል አስጎብኝተዋል።
ባለንበት የዲጂታል ዘመን የማህበረሰቡ የዲጂታል ተጠቃሚነት ማደግን ተከትሎ በዲጂታል ምህዳሩ ላይ እየጨመረ የመጣዉን የሳይበር ወንጀልን ለመከላከል ሀገራዊ የዲጂታልና የሳይበር ደህንነት ወንጀሎችን መመርመር የሚያስችል አቅም መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ በጉብኝቱ ወቅት ገልጸዋል።
ይህን ታሳቢ በማድረግ ኢመደአ ዘመኑን የዋጀ የዲጂታል ፎርንሲክና የሳይበር ወንጀል ምርመራ ማዕከል መገንባት መቻሉን ተናግረዋል። ይህም የሳይበር ወንጀሎችን በብቃት ከመመርመርና ፍትህን ከማረጋገጥ አኳያ ፋይዳው ጉልህ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስራዉ በተሟላ መልኩ ግቡን እንዲመታ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በቅንጅት መስራት ወሳኝ መሆኑን ወ/ሮ ትዕግስት ጠቁመዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸዉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ራሱን እያዘመነና በፎረንሲክ ዘርፍ ከፍተኛ አቅም እየገነባ መምጣቱን አንስተዉ በዲጂታል ምህዳሩ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመቀነስና ተጠያቂነትን ለመፍጠር የሁለቱ ተቋማት ሁሉን አቀፍ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
አሁን ባለዉ ነበራዊ ሁኔታ በተበታተነ መልኩ ስራዎችን መስራት አዋጭ አለመሆኑን ያነሱት ኮሚሽነር ጀነራሉ የፌደራል ፖሊስና ኢመደአ በተለይ በየዘርፋቸዉ የፈጠሩትን አቅም ለሌሎች በማካፈል፣በየተቋማቱ የሚገኘዉን የፎረንሲክ አቅም በጋራ የመጠቀም፣ ቴክኖሎጂዎችን ወደራስ አዉድ በማምጣትና በሰዉ ሃይል ልማት ዙሪያ በመስራት ቀጠናዊ ተጽዕኖ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።