ሀገር በቀል የደህንነት ማስጠበቂያ ምርቶች
ሀገር በቀል የደህንነት ማስጠበቂያ ምርቶች
* NISIR SIEM
* GASHA Anti-virus
* GASHA WAF
* GASHA VPN
* Enyuma IAM
* Code Protection
የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት እንዲሁም የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥንና እና የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል የሚያስችል ነው። ይህ የትራንስፎርሜሽን ጉዞ ግቡን እንዲመታ ደህንነቱ የተጠበቀ ዲጂታል ከባቢን መገንባትና የሳይበር ጥቃት ስጋቶችን መከላከል ወሳኝ ነው። ከዚህ አኳያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) #INSA የዲጂታል ኢትዮጵያን የትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማሳካትና ደህንነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሀገር በቀል የደህንነት ማስጠበቂያ ምርቶችን በማልማት እና የተለያዩ ተቋማትን በማስታጠቅ ላይ ይገኛል ።
ኢመደአ በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞና ውጥኖች ላይ ትኩረቱን አድርጎ በሳይንስ ሙዚዬም በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ ይዟቸው ከቀረቡት ሀገር በቀል የደህንነት ማስጠበቂያ ምርቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።
* ንስር (NISIR SIEM):- በኢመደአ ከለሙ የደህንነት ማስጠበቂያ ምርቶች መካከል አንዱ ንስር የተሰኘው የሴኪዩሪቲ ኢንፎርሜሽንና ኤቨንት አስተዳደር (Security Information and Event Management - SIEM) ሲሆን፤ ተቋማት የዲጂታል ሃብቶቻቸው ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶች ከመከሰታቸው በፊት ሊከሰቱ የሚችሉ የደህንነት ስጋቶችንና ተጋላጭነቶችን ለመከታተል እና አስፈላጊውን ምላሽ እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችል የደህንነት መፍትሄ ነው።
* ጋሻ ጸረ-ቫይረስ (GASHA AV):- እኩይ ሶፍትዌሮች ወደ ኮምፒውተሮችቻን እና ኔትዎርካችን ላይ እንዳይገቡ የሚለይ፣ የሚከላከል እና የሚያስወግድ የሳይበር ደህንነት ማስጠበቂያ መፍትሄ ነው።
* ጋሻ ፋየርወል (GASHA Web Application Firewall):- የዌብ አፕሊኬሽን ሲስተማችንን ከተለያዩ የሳይበር ጥቃቶችና ተጋላጭነቶች ለመጠበቅ የሚያስችል የደህንነት መፍትሄ ነው።
* ጋሻ ቪፒኤን (GASHA VPN):- ደህንነቱ የተጠበቀና ሚስጥራዊ የኢንተርኔት ግንኙነት ለማድረግ የሚያስችል የሳይበር ደህንነት ማስጠበቂያ መፍትሄ ነው።
* ኤኙማ የማንነት መለያና ማስተዳደሪያ (Enyuma Identity and Access Management - IAM):- ተቋማት የዲጂታል መሠረተ ልማቶቻቸውን እና ሃብቶቻቸውን በአግባቡ ለማስተዳደር እንዲሁም እነዚህን መሠረተ ልማቶችና ሃብቶች የተፈቀደለት አካል ብቻ መጠቀምና ማስተዳደር እንዲችል ለመፍቀድና ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው።
* ኮድ ፕሮቴክሽን (Code Protection):- የተለያዩ መተግበሪያዎች (Application) ከለሙ በኋላ በምልስ ምህንድስና (Reverse Engineering) ስሪታቸው እንዳይታወቅና ለሦሥተኛ ወገን ተላልፎ እንዳይሰጥ ለማድረግ የሚያስችል እንዲሁም የባለቤትነት መብትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የደህንነት ማስጠበቂያ አገልግሎት ነው።
የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞና ውጥኖች ላይ ያተኮረ ኤግዚቢሽን ጥር 19/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም መከፈቱ የሚታወስ ሲሆን፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ጨምሮ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ እና ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ምርትና አገልግሎቶቻቸውን በማሳየት ላይ ይገኛሉ።