ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ረቂቅ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ ተካሄደ
Publicador de Conteúdos e Mídias
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) “ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ” ረቂቅ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሄደ፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት፣ የመከላከያ ሚንስቴር፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የብሄራዊ ባንክ እና ሌሎችም መሰል የመንግስት ተቋማት ተሳታፊ ሆነዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ ባስተላለፉት መልእክት የሳይበር ምህዳሩ የሚያሳያቸው ለውጦች ፈጣን እና ኢ - ተገማች መሆናቸውን አንስተው ከዚህ አኳያ ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲያችን የሳይበር ምህዳሩ ላይ ከሚታየው እንቅስቃሴ እኩል የሚራመድ እና ለወቅቱ የሚመጥን እንዲሆን በማሰብ ረቂቅ ፖሊሲው መቀረጹን ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለው እንደተናገሩት ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ለማዘጋጀት ገፊ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል ሳይበር ድንበር ተሻጋሪ ክስተት መሆኑ እና ባህሪው ተለዋዋጭነት የሚታይበት መሆኑ፣ ሃገራችን እየተገበረችው ያለው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሳይበር ደህንነት በይበልጥ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑ፣ ከአየር ንብረት ቀጥሎ ትልቁ የአለም ስጋት የሳይበር ጥቃት እንደሆነ እያየን ያለበት ሁኔታ ላይ መሆናችን እንዲሁም የሳይበር ዲፕሎማሲያችንን ማሳደግ እና የዲጂታል ሉአላዊነታችንን ለማስጠበቅ ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲያችንን ወቅቱን ያመከለ አድረገን እንደንቀርፀው ትልቅ መነሻ ሆኖናል ሲሉ አብራርተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ድኤታ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ ባስተላለፉት መልዕክት የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የሁሉም አካላት ሃላፊነት መሆኑን እና ይህንንም ለማረጋገጥ ዜጎች፣ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍ እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ማወቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ በሃገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ጉዳይ እና ሃላፊነት አድርጎ እየሰራ ያለው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የቴክኖሎጂ እድገትን እና የሳይበር ተለዋዋጭ ባህሪን ያማከለ እንዲሁም ወቅቱን የሚመጥን ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ረቂቅ ማዘጋጀቱ ትልቅ እርምጃ መሆኑንም ሚኒስትር ድኤታው ገልጸዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላት የፖሊሲውን አስፈላጊነት ጠቅሰው ፖሊሲው ያሉበትን ክፍተቶች እና ሊይዛቸው ስለሚገባቸው ነጥቦች ከተቋማቸው ፍላጎት አንፃር የተለያዩ ሃሳቦችን እና ጥያቄዎችን ያንፀባረቁ ሲሆን ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይም ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡