ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የገነባችው አቅም በተሞክሮነት ሊወሰድ የሚችል እንደሆነ ተገለጸ
ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የገነባችው አቅም በተሞክሮነት ሊወሰድ የሚችል እንደሆነ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 19/2017 ዓ.ም፡- ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የገነባችው አቅም በተሞክሮነት ሊወሰድ የሚችል እንደሆነ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የሀገር መከላከያ እና ሰራዊት መልሶ ግንባታ ሚኒስትር ራማውክሰ ክሎድ ገለጹ፡፡
በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስትር የተመራ ልዑክ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን (ኢመደአ) ጎብኝቷል፡፡
የኢመደአ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት ለልዑካን ቡድኑ አቅባበል ያደረጉ ሲሆን በአስተዳደሩ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ገለጻ አድርገዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነቷን እና ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ተቋም በመገንባት ሂደት እየሰራችዉ ስላለዉ ስራ ለልዑካን ቡድኑ ገለጻ አድርገዋል።
በተለይም ሀገር በቀል የሆኑና ከፍተኛ የሆነ ክልከላ ያለባቸው የቴክኖሎጂ ምርቶች ላይ ጥናትና ምርምርም በማድረግ ረገድ የተገኙ ውጤቶች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር እንደ ተሞክሮ ሊወሰዱ የሚችሉ መሆኑን ልዑካን ተናግረዋል፡፡
የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስትር በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለመውሰድና በቀጣይ በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳለው የልዑካን ቡድኑ መሪ ራማውክሰ ክሎድ ገልጸዋል፡፡