አካታች የሆነ የዲጅታል ሽግግር ለማድረግ የዲጂታል መታወቂያ ሚና ከፍ ያለ መሆኑን የኢመደአ ዋና ዳይሬክተርና የID4Africa አምባሳደር ገለፁ
አካታች የሆነ የዲጅታል ሽግግር ለማድረግ የዲጂታል መታወቂያ ሚና ከፍ ያለ መሆኑን የኢመደአ ዋና ዳይሬክተርና የID4Africa አምባሳደር ገለፁ
አካታች የሆነ የዲጅታል ሽግግር ለማድረግ የዲጂታል መታወቂያ ሚና ከፍ ያለ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተርና የID4Africa አምባሳደር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ አስታወቁ፡፡
አይዲ ፎር ኢትዮጵያ #ID4Africa2025 ጉባኤ ላይ በተካሄደው የፓናል ውይይት ዋና ዳይሬክተሯ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተለይም የዲጂታል ሽግግርን ለማፋጠን እና በመላ ሀገሪቱ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እንደ ሀገር የዲጂታል ካዉንስል በማቋቋም ውጤታማ ስራዎች መሠራታቸውን ወ/ሮ ትዕግስት ተናግረዋል።
የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ፣ የዳታ መለዋወጫ ፕላትፎርም ግንባታ፣ የይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማት እንዲሁም የዳታ ማዕከሎች ግንባታ ዲጂታል ካውንስሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው ካሉት ውስጥ ተጠቃሽ እንደሆኑ ገልጸዋል።
እነዚህ የዲጂታል መሰረቶች የዜጎችን ተሳትፎ በማሳደግ፣ የኤሌክትሮኒክ ንግድ ስርዓትን በማመቻቸት እና የህዝብ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ እና አቅርቦትን በማሳለጥ ለሀገሪቱ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ስኬት መሰረታዊ መሆናቸዉን አስታውቀዋል።
የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ የስራ ድግግሞሽን በማስቀረት የሀብት ብክነትን የሚቀንስ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፤ አካታች የሆነ የዲጅታል ሽግግር ለማድረግ የዲጂታል መታወቂያ ሚናዉ ከፍ ያለ መሆኑን በመድረኩ አንስተዋል።
የዳታ መለዋወጫ ስርዓት /data exchange systems/ ለዲጂታል ኢትዮጵያ መሰረት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በመንግስት ተቋማት፣ በግሉ ዘርፍ እና በሌሎች ተቋማት መካከል መረጃዎችን በቀላሉ መለዋወጥ የሚያስችል በመሆኑ መንግስት መረጃን መሠረት ያደረገ ዉሳኔ እንዲስጥ ያግዘዋል ብለዋል ::
ለዚህም የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማሳያነት ጠቅሰዋል ::
“ሞሰብ” በአንድ ጣራ ስር የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን በተሳለጠ መልኩ እየሰጠ እንደሚገኝና የአሰራር ስርአቱ ዜጎች የተሟላ የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም የተለያዩ የፌዴራል ተቋማትን አገልግሎቶች በአንድ ጣራ ስር በቀላሉ እንዲያገኙ ማስቻሉን አብራርተዋል።
በሌላም በኩል እነዚህን ዲጂታል መሠረቶች ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች የላቁ ዉጤቶችን እያስገኙ ቢሆንም ተደራሽነቱን ለማስፋት ቀጣይ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል ::
በተለይም ደግሞ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ እያደገ የመጣዉን የሳይበር ጥቃት መቀነስ የሚያስችል አካሄድ እና የማህበረሰቡን የዲጂታል ንቃተ ህሊና ደረጃ ማሳደግ ላይ ቀጣይነት ያላቸዉ ስራዎች መስራት እንደሚገባ ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ገልጸዋል።
ለዲጂታል ሽግግሩ መሰረታዊ የሆኑ ስራዎች ሲሰሩ ከንድፈ ሃሳቡ ጀምሮ ለደህንነት ቅድሚያ በመስጠት (security by design) መርህ እየተሰሩ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ትዕግስት ይህም ሊፈጠሩ የሚችሉ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነቶችን በመቀነስ ሚስጥራዊነትን፣ ተደራሽነትን እና ምልዑነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።
እንደ ሀገርም ለኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር መሰረታዊያን በሆኑት የዲጂታል መታወቂያ፣ የክፍያ ስርዓት እና ይፋዊ ቁልፍ መሠረተ ልማት (PKI) ላይ ጠንካራ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ዲጂታል ስነ-ምህዳር ለመፍጠር የሚያስችል የሳይበር ደህንነት የቅድመ ጥንቃቄ ሞዴል መተግበሩን ጠቁመዋል።
በየትኛዉም የቴክኖሎጂ ልማቶቻችን ላይ የሳይበር ደህንነት ጉዳይን የስራዉ አካል አድርገን መስራት ከቻልን የተጋረጡብንን የጥቃት ተጋላጭነቶቻችን ከመቀነስ ባሻገር ዜጎች በመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያላቸዉን እምነት በማሳደግ እንደ ሀገር ከዘርፉ ማግኘት ያለብንን ጥቅም ለማግኘት ያስችለናል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሯ ወ /ሮ ትዕግስት ሀሚድ አብራርተዋል።