Asset Publisher

null ኢመደኤ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢመደኤ/ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮን የገቢ አሰባሰብ ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡

የኢመደኤ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ ስምምነቱ የዲጂታል ፕሮግራሞችን ለመተግበር እንዲሁም ደህንነታቸው የተጠበቁ ቴክኖሎጂዎችን ከማስታጠቅ አንጻር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመጀመሪያ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡

በኢመደኤ የለማው ደራሽ የተቀናጀ ፕላትፎርም የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የሚሰጠውን የግብር መሰብሰብ አገልግሎት ሥርዓት የሚያዘምን፣ የግብር ከፋዮችን እንግልት የሚያስቀር እንዲሁም የንግድ ተቋማት የዕርስ በርስ ግብይትና ሽያጭ በኦንላይን በማድረግ በየትኛውም ቦታ፣ በጊዜ ሳይገደቡና ሳይንገላቱ መፈጸም የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑን የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከዚህ በፊት ይጠቀምባቸው የነበሩ ሥርዓቶች ላይ የሳይበር ደህንነት ፍተሻና ግምገማ በማድረግ ክፍተቶችን የመሙላት እንዲሁም ወደፊት በሚታጠቋቸው ቴክኖሎጂዎች ላይም የደህንነት ፍተሻ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙልጌታ ተፈራ በበኩላቸው ስምምነቱ ፍትሃዊ፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለግብር ከፋዩ ህብረተሰብ በመስጠት ለከተማ አስተዳደሩ የሚያስፈልገውን ገቢ መሰብሰብ ነው ብለዋል፡፡

ቢሮው ከኤጀንሲው ጋር የሚኖረው መሠረታዊ ግንኙነትም በአንድ በኩል ከዚህ ቀደም የለሙ ቴክኖሎጂዎችን ደህንነት ተጠብቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ለማድረግ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በኢመደኤ የለሙ የቴክኖሎጂ ምርቶችን በተቋማቸው ተግባራዊ ለማድረግ እንደሆነ አቶ ሙልጌታ ገልጸዋል፡፡

በድምሩም ስምምነቱ የቢሮውን አገልግሎት አሠጣጥ ዘመናዊ በማድረግ ግብር ከፋዮች ግብሮቻውን በቀላሉ የሚያሳውቁበት እና የሚከፍሉበት እንዲሁም ከእንግልት ነጻ በሆነና ግልጸኝነት ባለው አግባብ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችላቸውም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡