Asset Publisher

null ኢመደኤ ለተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ወኪል ድርጅቶች ስልጠና ሰጠ

 

አዲስ አበባ፡ ጥር 25/2014፡- የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢመደኤ/ በሀገሪቱ ለሚንቀሳቀሱ የተባበሩት መንግስታት ወኪል ድርጅቶች የመረጃ፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ምርቶችን ወደ ሀገር ዉስጥ ለማስገባት ሲፈልጉ ሊከተሏቸዉ ስለሚገቡ ጉዳዮች ስልጠና ሰጥቷል።

 

ኢመደኤ የሀገሪቱ የኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማቶችን ደህንነት ለማረጋገጥ በግለሰቦች፣ በመንግስታዊም እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ የመረጃ፣ የመገናኛ እና የኮሙዩኒኬሽ ምርቶች ላይ የሴኪዩሪቲ ክሊራንስ ስራዎችን እንደሚሰራ ይታወቃል።

ኤጀንሲዉ ይህን ተግባር ሲያከናውን ቴክኖሎጂውን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት የሚፈልጉ አካላት በተዘጋጀ የማመልከቻ ድረገጽ በምን መልኩ ማመልክት እንዳለባቸው እና ህግና ስርአትን ተከትሎ መጠቀም ላይ በሁሉም አካላት ላይ ክፍተት እየታየ በመገኘቱ ስልጠናው መዘጋጀቱን ተጠቁሟል፡፡

 

ክፍተቱን መሠረት በማድረግም ኢመደኤ በዘርፉ ለተሰማሩ ግለሰቦች፣ የሀገር ዉስጥ የግልና የመንግስት ተቋማት እንዲሁም መንግስዊ ያለሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቴክኒካል እና ህጋዊ አሠራር ላይ ስልጠና እየሠጠ ይገኛል፡፡

በዛሬው ዕለትም ከተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ወኪል ድርጅቶች ለመጡ ሙያተኞች በበይነ-መረብ በቀጥታ ወደ ሀገር የሚያስገቧቸውን ምርቶች በምን መልኩ ማሳወቅ፣ ማስመዘገብ እና ፍቃድ ማግኘት እንደሚችሉ፤ ፍቃድ ካገኙ በኋላ በምን መልኩ ምርቶቹን መጠቀም እንደሚገባቸዉ እንዲሁም በቴክኒካል እና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የግማሽ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡