ኢመደአ የዲጂታል ፎረንሲክ ድሕረ ምረቃ ሰርተፊኬት ፕሮግራም የማስተማሪያ ሞጁል አዘጋጅቶ ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ
ኢመደአ የዲጂታል ፎረንሲክ ድሕረ ምረቃ ሰርተፊኬት ፕሮግራም የማስተማሪያ ሞጁል አዘጋጅቶ ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የዲጂታል ፎረንሲክ ድሕረ ምረቃ ሰርተፊኬት ፕሮግራም የማስተማሪያ ሞጁል አዘጋጅቶ ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ፡፡ ርክክቡን የኢመደአ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ም/ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ አከናውነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ም/ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት በዲጂታል ምህዳር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በመጠንም ሆነ በአይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመሩ መምጣታቸውን ገልጸው እነዚህን ወንጀሎች ለመመርመርና ለፍትሕ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም መገንባት ለሀገራዊ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እየሰጠ ለሚገኘው የዲጂታል ፎረንሲክ የድሕረ ምረቃ ሰርተፊኬት ፕሮግራም የማስተማሪያ ሞጁል በኢመደአ በኩል መዘጋጀቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ብቁ የሆነ የሰው ሃይል ለማልማት ትልቅ አቅም የሚፈጥር እንደሆነ ም/ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ ተናግረዋል፡፡
የኢመደአ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውሰው፤ በዛሬው እለት የተከናወነው የዲጂታል ፎረንሲክ ድሕረ ምረቃ ሰርተፊኬት ፕሮግራም የማስተማሪያ ሞጁል ርክክብ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅታዊ ሥራ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ፈጣን ዕድገት ለዲጂታል ፎረንሲክ ምርመራ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን የገለጹት አቶ ዳንኤል፤ ከእነዚህ የቴክኖሎጂ ዕድገቶች ጋር እኩል መሄድ አስፈላጊ የሆኑ ክህሎቶችን እና መሳሪያዎችን በመታጠቅ ውጤታማ ምርመራዎችን ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም ሀገራዊ የዲጂታል ፎረንሲክ አቅም ዳሰሳ ጥናት መከናወኑን ያስታወሱት አቶ ዳንኤል ጉታ፤ በጥናቱ ከተለዩ ቁልፍ ክፍተቶች መካከል የዲጂታል ፎረንሲክ ምርመራን ለማከናወን የሚያስችል የሰው ሃይል አቅም አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ኢመደአ በመቋቋሚያ አዋጁ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የፍትህ አካላት የዲጂታል ፎረንሲክ ምርመራ አቅም እንዲፈጥሩ ድጋፍ የማድረግ እና አስፈላጊ የምርመራ ቴክኖሎጂዎችን የማቅረብ፣ እንዲሁም ዘርፉን ለመምራት የሚያስችሉ ደንብና መመሪያዎችን የማውጣት ሃላፊነት መሰረት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ለጀመረው የዲጂታል ፎረንሲክ ድሕረ ምረቃ ሰርተፊኬት ፕሮግራም የማስተማሪያ ሞጁል ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
በሀገራችን ከሚፈጸሙ የሳይበር ወንጀሎች መጠንና ስፋት አኳያ ሀገራዊ የዲጂታል ፎረንሲክ ምርመራ አቅም በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በየደረጃው መገንባት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ ዳንኤል ከዚሁ ጎን ለጎንም ብቁ የሰው ሃይል ማልማት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡