2ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ይጀምራል

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

አዲስ አበባ፡ መስከረም 27/2014፡- በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢመደኤ/ አዘጋጅነት በየዓመቱ በጥቅምት ወር የሚከበረው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ዘንድሮም ከጥቅምት 1 እስከ 30/ 2014 ዓ.ም እንደሚከበር ተገለጸ፡፡

2ኛውን የሳይበር ደህንነት ወር አስመልክቶ የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸው የዘንድሮው የሳይበር ደህንነት ወር "የሳይበር ደህንነት የጋራ ኃላፊነት ነው! እንወቅ! እንጠንቀቅ!" በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ገልፀዋል፡፡

2ኛው የሳይበር ደህንነት ወር የሚከበርበት ዋና ዓላማም የሳይበር ማህበረሰቡን እና ተቋማትን የሳይበር ደህንነት ንቃተ-ህሊና ለማጎልበት የሚያስችል ንቅናቄን በማካሄድ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን የማስጠበቅ ተልዕኮ ማገዝ መሆኑን ዶ/ር ሹመቴ ገልጸዋል፡፡

በዚህ የሳይበር ደህንነት ወር የዜጎችንና የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ንቃተ-ህሊና ለመገንባት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑም ዶ/ር ሹመቴ ተናግረዋል፡፡

በሀገራችን የዜጎች ሆነ የተቋማት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ከማደጉ ጋር ተያይዞ በዜጎች፣ በተቋማት እንዲሁም በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በተለይም ሀገራችን ባለችበት ወቅታዊ የደህንነት ሁኔታ የጥቃት ዒላማ ልትሆን የምትችልበት ዕድል ሰፊ በመሆኑ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ መከላከል ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥም ሙያዊ ስነ-ምግባርና ክህሎት የተላበሰ የሰው ኃይል ማፍራት፣ ትክክለኛ ቴክኖሎጂ መጠቀም እና በህግ ማዕቀፎች መታገዝ መሠረታዊ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በዚህ የሳይበር ወርም ከ300 በላይ የሚሆኑ የሚመለከታቸው ተቋማት እንደሚሳተፉ፣ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሑፎችና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንደሚካሄዱ ተገልጿል፡፡

2ኛው የሳይበር ደህንነት ወር በማስመልከት ጥቅምት 1 ቀን 2014 ዓ.ም በሸራተን ሆቴል የሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ እንደሚከፈት እና ወሩን ሙሉ በኢመደኤ ዋና መ/ቤት በሚዘጋጅ አውደርዕይ እና ወርክሾፖች እንደሚከበርም ዶ/ር ሹመቴ ገልጸዋል፡፡

በኤግዚብሽንና በወርክሾፖች ላይ ከሁሉም ሚንስቴር መ/ቤቶች፣ ከሚዲያ ተቋማት፣ ከፀጥታና ደህንነት ተቋማት፣ ከህ/ተ/ም/ቤት፣ ከፋይናንስ ተቋማት፣ ከቁልፍ የመንግሰት መሠረተ ልማት እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ከተሰማሩ ተቋማት የሚመጡ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ሙያተኞች እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል በቅርቡ በኢትዮጵያ ብርድካስቲንግ ኮርፖሬሽን /EBC/ ፌስቡክ ገጽ ላይ የጋጠመው ችግር መጣራት እየተደረገበት እንደሚገኝ ገልፀው አስከአሁን ባለው ምርመራ ችግሩ ከውስጥ ባሉ ባለሙያዎች ክፍተት የተፈጠረ እንደሆነ አዝማሚያዎቹ እንደሚያሳዩ ገልፀው በቀጣይ ሙሉ ምርመራው ሲጠናቀቅ ይፋ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

የሳይበር ደህንነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ እንደሚከበር ታውቋል፡፡‹