የፋይናንስ ተቋማት ቀዳሚ የሳይበር ጥቃት ዒላማዎች በመሆናቸው ለሳይበር ደህንነት ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

[#if smallImage??]
  [#if smallImage?is_hash]
    [#if smallImage.alt??]
      ${smallImage.alt}
    [/#if]
  [/#if]
[/#if]

 

2ኛውን ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወርን ምክንያት በማድረግ ከፋይናንስ ተቋማት ለመጡ የሥራ ኃላፊዎች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በመክፈቻው መርሃግብር የተገኙት የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው እንደገለጹት በሀገራችን ላይ ከሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች በመሆናቸው የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም ብቻ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ዓመታት በተለየ መልኩ ከፍተኛ መጠን ያለው የሳይበር ጥቃቶች በሀገራችን ላይ ሙከራ መደረጋቸዉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህ ቁጥር መጨመር ሀገራዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ጨምሮ አካባቢዊ፣ ቀጠናዊና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖዎች ከዋና ምክንያቶች መካከል መሆናቸውንም አመላክተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የተሰነዘሩትን ጥቃቶች እንደ ሀገር መከላከል ባይቻል ኖሮ አሁን ላይ ለመገመት አዳጋች የሆኑ ጉዳቶች በሀገር ኢኮኖሚና ሰላም ላይ ያሳርፉ ነበረም ብለዋል፡፡

በመሆኑም በየጊዜው ቁጥሩ እና ዓይነቱ እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት አንድ እርምጃ ወደፊት በመቅደም መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ለዚህም በተለይ የሰው ኃይል ማብቃት፣ ወቅቱ የሚጠይቃቸውን ቴክኖሎጂዎች መታጠቅ እና የአሠራር ሥርዓቶች መዘርጋት ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

 

ዶ/ር ሹመቴ በንግግራቸው ማብቂያ ኤጀንሲው እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ 24 ሰዓት የፋይናንስ ተቋማቱን ለመደገፍ እና አስፈላጊ በሆኑ ቴክኒካል ጉዳዮችም እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በኢመደኤ የሳይበር ጥቃት ትንተና ባለሙያ አቶ አበባው ዘውዱ በሳይበር ደህንነት ምንነትና ባህሪያት፣ በሳይበር ጥቃት ዓይነቶችና ባህሪያት፣ የሳይበር ምህዳሩ በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያመጣው መልካም እና አሉታዊ አጋጣሚዎች እንዲሁም ከተቋማቱ ምን እንደሚጠበቁ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በዕለቱ የተገኙ ተሳታፊዎችም ከዚህ ቀደም ከኢመደኤ ጋር ስለነበራቸዉ የጋራ ጉዳዮች፣ በአሁኑ ወቅት እያገጠሟቸው ባሉ ተግዳሮቶች እና በቀጣይ በትብብር ሊሠሩባቸዉ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎች እና ሀሳቦችን አቅርበው ከመደረክ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

"የሳይበር ደህንነት የጋራ ኃላፊነት! እንወቅ፣ እንጠንቀቅ!" በሚል መሪ ቃል 2ኛው በሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር በኢመደኤ አዘጋጅነት እየተከበረ ይገኛል፡፡