ኢመደአ ለአዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ

[#if smallImage??]
  [#if smallImage?is_hash]
    [#if smallImage.alt??]
      ${smallImage.alt}
    [/#if]
  [/#if]
[/#if]

 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር /ኢመደአ/ ለአዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች እየተሰጠ በሚገኘው የሥልጠና መርሃግብር ላይ በመገኘት በሳይበር ደህንነት መሠረታዊ ጽንሰ ሀሳቦች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

በሥልጠና መርሃ ግብሩ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ስለሳይበር ደህንነት ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እድገት አወንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖዎች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተለይም በሳይበር ዲፕሎማሲ ሀገራችን ከአዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ምን እንደምትጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

 

በኢመደአ የሳይበር ደህንነት አስተዳደር ማዕከል ሃላፊ አቶ ፍጹም ወስኔ የሳይበር ደህንነት ምንነትና ባህሪያት እንዲሁም ሊወሰዱ በሚገቡ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች ዙሪያ ለአምባሳደሮቹ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በተለይም የዲፕሎማቲክ ተቋሞቻችን የሳይበር ደህንነታቸውን ማስጠበቅ እንዳለባቸው እና ሀገራዊ ፍላጎት በሳይበር ደህንነት ዲፕሎማሲ ዙረያ ምን ጉዳዮችን እንደያዙ አቶ ፍጹም አብራርተዋል፡፡

የዲፕሎማቲክ ተቋማቾችን ከሳይበር ጥቃት ለመጠበቅም አመራሮች ለሳይበር ደህንነት ኃላፊነት መውሰድ፣ አስፈላጊውን የሰው ኃይልና በጀት መመደብ፣ መዋቅር በተቋሞቹ ውስጥ መፍጠር፣ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እና የሳይበር ቴክኖሎጂዎችን መታጠቅ እንደሚጠበቅባቸው አቶ ፍጹም አስረድተዋል፡፡

 

ከዚህ ባለፈም ከተለያየ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገራት ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ስትራቴጂክ አጋርነት እና ትብበር መፍጠር እንደሚገባ እንዲሁም የሳይበር ደህንነት ዲፕሎማሲ የትኩረት መስኮችን በዝርዝር በማቅረብ በሳይበር ምህዳሩ የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዘመናዊ የዲፕሎማሲ ስራን ይበልጥ ዉጤታማ ለማድረግ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

አምባሳደሯ በቀጣይም ሚኒስቴር መ/ቤታቸው ከአስተዳደሩ ጋር በመተባበር በተለያዩ ደረጃዎች ለሚገኙ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ወቅታዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች ለመስጠት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በተለያዩ አገራት ኢትዮጵያን እንዲወክሉ ለተሾሙ አዲስ አምባሳደሮች ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት የተለያዩ ሥልጠናዎች ሲሰጡ እንደቆየ ይታወቃል፡፡