ኢመደአ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ወጣቶች እየደገፈ እንደሚገኝ ተገለጸ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

 

አዲስ አበባ ሚያዚያ 8/2014 ዓ/ም ፡- በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ወጣቶች በመደገፍ አቅማቸውን የሚያሳድጉበትንና ራሳቸውም ሆነ አገራቸው የሚጠቅሙበትን ምቹ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) አስታወቀ።

የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ኢመደአ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ፍላጎትና ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ልጆች በማሰልጠን እንዲሁም ከስራው ጋር ትውውቅ እንዲያደርጉ እድል በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል። ወጣቶችን በመደገፍ አቅማቸውን የሚያሳድጉበትንና ራሳቸውንና አገራቸውን የሚጠቅሙበት ሁኔታ እንዲፈጥሩ ማድረግ ይገባል፤ ለዚህም የሥራ እድል ፈጠራ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችና ተቋማት ለወጣቶቹ ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎችን የመደገፍ ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት ዶክተር ሹመቴ ፤የሚመለከታቸው አካላትና ባለሀብቶች ልዩ ተሰጥዖና ችሎታ ያላቸውን ሰዎች በመደገፍ በጋራ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ሊፈጥሩ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ላይ ተስፋ የሚጣልባቸው ፈጠራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት ዶክተር ሹመቴ፤ በጤና፣ ግብርና፣ በኢንዱስትሪና በሳይበር ነክ መስኮች የሚሠሩ ወጣቶችን ችሎታቸውንና ፈጠራቸውን መተግበር የሚችሉበት እድል ሊመቻችላቸው እንደሚገባም ገልጸዋል።

በመንግሥት በኩል ወጣቶችን ማበረታታትና የመደገፍ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሹመቴ፤ በዚህ ረገድ ኢመደአ በሳይበር ደህንነትና ተዛማጅ ዘርፎች ላይ ፍላጎት ያላቸውን በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በማሰጠልንና በማስተማር የማበረታታትና የመደገፍ ተግባራትን መጀመሩን ተናግረዋል።

ዶክተር ሹመቴ እንደገለጹት፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር “ሳይበር ቻሌንጅ” በሚባል ፕሮግራሙ አማካኝነት የኢንተርኔት እድል ያላቸውን ወጣቶች የማብቃት ሥራ እየሠራ ይገኛል።

የሳይበር ደህንነት ዘርፉ ተለዋዋጭና መገመት የማይችል እየሆነ እየመጣ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ጦርነት፣ እገታ፣ ዲፕሎማሲ እንዲሁም የማኅበራዊ ስነ-ተግባቦት በሙሉ ዲጂታል እየሆኑ በመምጣታቸው ምክንያት ከስር መሠረቱ መረጃ ሀብት የሆነበት ዘመን በመሆኑ በዘርፉ ያሉትን ተዋናዮች ማበረታታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል።

ኢመደአ በትምህርት ደረጃ ያልተገደበ ፕሮግራሚንግ ፣ሀኪንግና ሌሎችም ዘርፎች ላይ ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች ተሰጥዖን የማልማት ሥራ በመከወን ላይ ይገኛል ያሉት ዶክተር ሹመቴ፤ በመጀመሪያው ዙር 42 እንዲሁም በሁለተኛው ዙር 37 ሰልጣኞችን ማሰልጠኑን ተናግረዋል።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሰለጠኑት ወጣቶች በዓለም አቀፍ ተቋማት በሳይበር ደህንነት የሥራ መስኮች ተቀጥረው የመሥራት እድል ሊኖራቸው እንደሚችል የጠቆሙት ዶክተር ሹመቴ፤ ለማይክሮሶፍት፣ ጎግልና በአገር ውስጥም በባንኮችና በኢንሹራንሶች የመቀጠር እድል እንዳላቸውም ተናግረዋል።