ወደ ሀገር እንዳይገቡ የተከለከሉ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ቁጥር ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ
ወደ ሀገር እንዳይገቡ የተከለከሉ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ቁጥር ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ
ወደ ሀገር እንዳይገቡ የተከለከሉ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ቁጥር ከ2013 በጀት አመት ጋር ሲነፃፀር 23 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ፡፡
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የመረጃና መገኛና ቴክኖሎጂ ዲቪዥን ሀላፊ አቶ እሸቱ ቡሬሳ እንደገለፁት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ክልከላ ከተደረገባቸው የመረጃ የመገናኛና የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች መካከል ላልተገባ ተግባር የሚውሉ የስለላ ካሜራዎች፣ ከፍተኛ የስጋት ደረጃ ያለው እና የጉዳት መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ለስለላ እና ለተለያዩ የሽብር ጥቃት የሚውሉ ድሮኖች፣ ከኢትዮጵያ ቴሌኮም ቁጥጥር ውጪ የሆነ የሳተላይት ስልኮች፣ ጂ.ፕ.ኤሶች፣ የሬድዮ መገናኛዎች፣ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ሊያደርስ የሚችል ቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎች፣ ከፍተኛ አቅም ያላቸው የማይኒንግ ሰርቨሮች (mining server ) እና የጦር ሜዳ አጉሊ መነፅር (ባይናኩላር) በዋናነት እንደሚገኙበት አቶ እሸቱ ገልጸዋል፡፡
በ2014 በጀት ዓመት ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በአካል እና በሲስተም (Online) 754 ተቋማት እና ድርጅቶችን አስተናግዷል፡፡
ከነዚህም ተቋማት እና ድርጅቶች መካከል 690 የሚሆኑት ተቋማት እና ድርጅቶች ሰባ ሰባት ሺ ሶስት መቶ ሃምሳ (77,350) የመረጃና የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በማስገባት በኢመደአ ቁጥጥር ሂደት ውስጥ ሆነው ለመገልገል ውል በመፈፀም ፍቃድ የተሰጣቸው ሲሆን ስልሳ አራት (64) ተቋማት እና ድርጅቶች ደግሞ ሶስት ሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ስምንት (3‚998) የሚሆኑ የመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ ክልከላ ተደርጎባቸዋል፡፡
በዚህም በ2014 በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ ወደ ሀገር እንዳይገቡ የተከለከሉ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ቁጥር ከአምናው 2013 በጀት አመት ጋር ሲነፃፀር 23% ጭማሪ ማሳየቱን አቶ እሸቱ አብራርተዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከተሰጡት ተልእዎች ውስጥ ኢንፎርሜሽን መሰረተ-ልማት ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም በመገንባት ብሄራዊ ጥቅሞችን ማስጠበቅ ነው፡፡ይህን ተልእኮውን እውን ከማድረግ አንጻር በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ምዝገባ እና ቁጥጥር ማድረግ አንዱ ነው፡፡
በዚህም ባሳለፍነው በ2014 በጀት ዓመት አስተዳደሩ ባካሄደው የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ምዝገባ አጠቃላይ ሃያ አምስት ሺ ስድስት (25,006) የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ምዝገባ መካሄዱን አቶ እሸቱ ገልጸዋል፡፡
አስተዳደሩ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ምዝገባ ማካሄዱ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በህጋዊና በህገወጥ መንገድ የሚጠቀሙትን ለመለየት፤ በሀገር ደረጃ ስጋት የሚሆኑትን የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር፤ ተጠቃሚው የሚጠቀምባቸውን የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ጉዳትና ጥቅሙን ለይቶ በማወቅ ለመቆጣጠር እንዲችል እና ለሶስተኛ ወገን እንዳያስተላልፍ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ በሀገር ደረጃ የቴክኖሎጂ ሥርጭትን በመለየት እንደ አስፈላጊነቱ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች መቆጣጠሪያ ቢሮ በመክፈት ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ፤ ለሚመለከታቸው ተቋማትና አካላት ስለመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ጥቅምና ጉዳት በጥልቀት ስልጠና ለመስጠት፤ብሎም የሙያተኛን አቅም ለማጎልበትም እንደሆነ አቶ እሸቱ አብራርተዋል፡፡
የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በአግባቡ ቁጥጥር ካልተደረገባቸው እና በህገ ወጥ አካላት እጅ ቢገኙ በሀገር ደረጃ የሚያስከትሉት ጉዳት እና ስጋት በጣም ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ግለሰቦች፣ ተቋማትና መንግስታዊ አካላት አስፈላጊውን ጥንቃቄና ክትትል እንዲያደርጉ አቶ እሸቱ መልዕክታቸውን አስተላላፈዋል ፡፡