የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ለሳይበር ደህንነት የሚጫወተው ሚና በሚል ርዕስ ኮንፍረንስ ተካሄደ
የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ለሳይበር ደህንነት የሚጫወተው ሚና በሚል ርዕስ ኮንፍረንስ ተካሄደ
የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ለሳይበር ደህንነት የሚጫወተው ሚና በሚል ርዕስ በመላ ሀገሪቱ ከሚገኙ ተማሪዎች እና የአካዳሚክ ማኅበረሰቡ ጋር የቪዲዮ ኮንፍረስን (Video Conference) የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡
የውይይት መድረኩን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አርአያሥላሴ ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬት የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ እና የሳይበር ደህንነት አስቻይ የሆነ ሚናን ይጫወታሉ ብለዋል፡፡
ባለንበት የዲጂታል ዘመን በየትኛውም የሙያ መስክ ላይ ብንሰማራ የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ከሌለን ተወዳዳሪ መሆን አንችልም፤ ከዚህ አኳያ አጠቃላይ የቴክኖሎጂ ክህሎታችንን ማዳበር ለነገው ዓለም እራስን ማዘጋጀት እንደሆነ ልናሰምርበት ሲሉ አቶ ዮዳሄ በመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት ጠቅሰዋል፡፡ በሌላም በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃም ይሁን እንደ ሀገር አጠቃላይ ሕይወታችን ዲጂታላይዝድ በሆነ ቁጥር የሳይበር ጥቃት ስጋትም የዛኑ ያህል እያደገና እየተወሳሰበ ይመጣል፤ በመሆኑም በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ያለንን ግንዛቤና ንቃተ ሕሊና ደረጃም በዚያው ልክ ማጎልበት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በመላ ሀገራችን የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዲሁም የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች “የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ” ኢኒሼቲቭ የቀረቡ ስልጠናዎችን በመውሰድ በዓለም አቀፍ ደረጃ እራሳቸውን ብቁና ተወዳዳሪ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አቶ ዮዳሄ አርአያሥላሴ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዛሬው እለት የተካሄደው ኮንፍረንስ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 5ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር አካል ነው፡፡