ለዲጂታል ሚዲያ አስተዳዳሪዎችና ባለሙያዎች በዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ ነው
ለዲጂታል ሚዲያ አስተዳዳሪዎችና ባለሙያዎች በዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ ነው
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እና ሜታ ኩባንያ በጋራ በመሆን ከተለያዩ የፌደራል መንግሥት ተቋማት፣ ሚኒስቴር መ/ቤቶች እና የመንግሥት ሚዲያ ተቋማት ለመጡ የዲጂታል ሚዲያ አስተዳዳሪዎች እና ባለሙያዎች በዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
በስልጠናዉ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢመደአ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ እንደገለጹት ኢመደአ እና ሜታ ይህን ስልጠና ያዘጋጁት በሀገራችን ያለውን የዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀም እና ደህንነት ለማሻሻል ነው ብለዋል።
የማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚነታች ከጊዜ ወደጊዜ በፍጥነት እያደገ መሆኑን ያነሱት አቶ ዳንኤል እንደ ፌስቡክ ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞች ለመንግሥት ግንኙነት፣ ለሚዲያ ተሳትፎ እና ለህዝብ ግንኙነት ሥራ ጠቃሚ መሣሪያዎች ሆነው እያገለገሉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም መረጃዎችን ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ፤ ግልጽነትን ለመፍጠርና በመንግስትና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነትና ትስስር በማጎልበት ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ነገር ግን ፌስቡክን ጨምሮ ሌሎች የማሕበራዊ ሚዲያዎችን ደህንነታቸዉ በተጠበቀ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም የሚዲያዎቹን ባሕሪና ማሕበረሰባዊ ደንቦችን ጠንቅቆ ማወቅና መከተል አስፈላጊ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የማህበራዊ ሚዲያ ደንቦች አለማወቅና አለመተግበር የተለያዩ ችግሮችን እያስከተ ነዉ ያሉት አቶ ዳንኤል ከእነዚህ መካከልም የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች መታገድ፣ የእይታ መጠን መቀነስ፣የይዘት መወገድ ወ.ዘ.ተ በስፋት እየተስተዋሉ መሆኑን ገልጸዋል። ሁለቱ ተቋማት ይህን ስልጠና ሲያዘጋጁም እንደ ተቋም የምንጠቀማቸውን የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾች ደህንነታቸውን በጠበቀ መልኩ በውጤታማነት ለመጠቀም የሚያስችሉ መሰረታዊ ግንዛቤዎች ለመፍጠር ታሳቢ አድርጎ መሆኑን ተናግረዋል።